የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለሲዳማ እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የስልጠና እና የውይይት መድረኮችን በሻሸመኔ ከተማ ከመስከረም 8 እስከ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዲሁም በሃዋሳ ከተማ ከመስከረም 11 እስከ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. አካሂዷል። መድረኮቹ የተሳታፊዎችን የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ በማሳደግ የክትትልና ቁጥጥር ዐቅማቸውን ለማጎልበት ያለሙ ናቸው።
በመድረኮቹ የምክር ቤቶቹ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እና እንዲሟሉ ከማድረግ አንጻር ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በተመለከተ የሌሎች ሀገራት ምክር ቤቶችን ተሞክሮ እንዲሁም የፌዴራልና የክልሎቹን ሕጎች በማጣቀስ ውይይት ተካሂዷል፡፡ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በሚሠሩበት ወቅት ይህንኑ ታሳቢ አድርገው ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተመላክቷል። በተጨማሪም ከሰብአዊ መብቶች ጋር የተያያዙ የመንግሥት ግዴታዎች፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅት ስለሚተገበሩ ክልከላዎችና ግዴታዎች እንዲሁም ሊጠበቁ የሚገባቸው የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና መርሖች ላይ ገለጻ ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል የምክር ቤት አባላቱ በየክልላቸው ለሚያከናውኑት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ አጋዥ የሚሆን በኮሚሽኑ የተዘጋጀ የሰብአዊ መብቶች የማረጋገጫ መዘርዝር (Checklist) ቀርቦ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። እንዲሁም በክልሎቹ በ2015 ዓ.ም. ኢሰመኮ ባከናወናቸው የማረሚያ ቤቶች እና የፖሊስ ጣቢያዎች ክትትልና ምርመራ ሥራዎች ሪፖርት የተለዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሊታረሙ ስለሚችሉበት አግባብ ተሳታፊዎች ተወያይተዋል።
የምክር ቤት አባላቱ በየክልሎቹ የተለዩት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በቋሚ ኮሚቴዎቹ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች በተወሰነ መልኩ የተለዩ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸው ከበጀት፣ ከሕግ ክፍተቶች፣ ከአሠራር ችግሮች እና ከአፈጻጸም ጉድለቶች የመነጩ መሆናቸውን አስረድተዋል። አክለውም በጀት የመወሰን፣ ሕግ የማውጣት እና ቁጥጥር የማካሄድ ሥልጣናቸውን በመጠቀም እንዲሁም ከመድረኮቹ ባገኙት ግንዛቤና የሰብአዊ መብቶች ማረጋገጫ መዘርዝር በመታገዝ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በመድረኮቹ ማጠቃለያዎች ላይ የኢሰመኮ ሃዋሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በጋሻው እሸቱ ምክር ቤቶች ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መስፋፋት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።