በደቡብ ክልል፣ የኮንሶ ዞን ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ዳግም ባገረሹ ተከታታይ ግጭቶች የደረሰው አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት፤ የአካባቢው ሰብአዊ ቀውስ ዘላቂ እልባት ባለማግኘቱ እየተባባሰ መሄዱን እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ። 

ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ከኅዳር 12 ቀን እስከ ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በሀይበና እና በአይዴ ቀበሌዎች፣ በአርባምንጭ፣ በጊዶሌ እና በካራት ከተማዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት የፈጣን ዳሰሳ ሪፖርት ነው (ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በኮንሶ ዞን አካባቢ ባገረሸው ግጭት መነሻነት በአካባቢው ስላለው ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ የተደረገ ፈጣን ምርመራ ሪፖርት) ። 

በሪፖርቱ እንደተመለከተው ቢያንስ 66 ሰዎች ተገድለዋል፣ 39 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ብዙ ቤቶችና ንብረት በእሳት ተቃጥለዋል እንዲሁም ከመቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹የኮንሶ ዞን እና አካባቢው ረዘም ላለ ጊዜ ሰላም አጥቶ የቆየበት ችግር ተገቢውን ትኩረት አላገኘም። በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ከመኖሪያው መፈናቀሉና ከመካከላቸው ለአምስተኛ ጊዜ የተፈናቀሉ ተጎጂዎች ጭምር መኖራቸው አሳዛኝ የሰብአዊ መብቶች ቀውስ ነው። ስለሆነም ለተፈናቃዮች በአፋጣኝ አስፈላጊውን ድጋፍ ከማቅረብ ባሻገር፣ የፌዴራሉና የክልሉ መንግሥታት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ተቀናጅተው ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍን መፍትሄ ሊሰጡ ይገባል›› ብለዋል።

ዝርዝር ሪፖርቱን እዚህ ያግኙ፦ ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በኮንሶ ዞን አካባቢ ባገረሸ ግጭት መነሻነት በአካባቢው ስላለው ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ የተደረገ ፈጣን ምርመራ ሪፖርት