የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሻሻል እንዲሁም የተለያዩ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን ልዩ ፍላጎትና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ ውይይት ታኅሣሥ 14 እና 15 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይት መድረኩ ከፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከሐረሪ፣ እና ከሲዳማ ክልሎች የተውጣጡ የፍትሕ ቢሮ ተወካዮች፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕግ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ የፍትሕ ተደራሽነትንና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ከማረጋገጥ አንጻር ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ሚና፣ በሀገራዊ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ የተቀመጡ መመዘኛዎች እና ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ገለጻ ቀርቧል። የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ በረቂቁ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሰጡ አስተያየቶችና በአርቃቂ ቡድኑ የተወሰዱ ማሻሻያዎች ላይ ውይይት ተደርጓል። በተጨማሪምነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ፣ ተደራሽ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በኢሰመኮ አስተባባሪነት በተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚቴ የተረቀቀውን እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚተገበረውን ረቂቅ የድርጊት መርኃ ግብር በመገምገምና በማጠናቀቅ ወደ ተግባር በሚገባበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ላይ በቅድመ ችሎት፣ በማረሚያ ቤቶች እና በሴቶች ሰብአዊ መብቶች ላይ ልምድ ያላቸው እንደ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች፣ ሴንተር ፎር ጀስቲስ እና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኀበር ያሉ ሲቪል ማኅበራት አዳዲስ አሠራሮችን፣ የሥራ መምሪያዎችንና ጥናቶችን መሠረት በማድረግ ልምዳቸውን አካፍለዋል።

የኢሰመኮ ፕሮግራምና አጋርነት ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ማንያውቃል መኮንን የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል በአገልግሎት ሰጪዎችና በባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ አክለውም ኢሰመኮ የፍትሕ ተደራሽነትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥና ለውጥ ለማምጣት ነጻ የሕግ ድጋፍ ላይ ከሚሠሩ አጋሮች ጋር በትብብር መሥራቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።