የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃና ድጋፍን አስመልክቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጸደቀው የካምፓላ ስምምነት ማስፈጸሚያ ረቂቅ ብሔራዊ ሕግ ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ጥቅምት 29 እና 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በሱሉልታ ከተማ ተወያይቷል። ውይይቱ የካምፓላ ስምምነት ማስፈጸሚያ ሕግ አለመኖር በተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ድጋፍ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ፣ በስምምነቱ ማስፈጸሚያ ብሔራዊ ሕግ ሊካተቱ የሚገባቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እንዲሁም ብሔራዊ ሕጉን የማርቀቅ ሂደት የሚገኝበት ደረጃ ላይ ያተኮረ ነበር።
በውይይት መድረኩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች፣ የዲሞክራሲ ጉዳዮች፣ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች፣ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች እንዲሁም የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ጥበቃና ድጋፍን አስመልክቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የካምፓላ ስምምነት ምንነት፣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የካምፓላ ስምምነት ተዋዋይ ሀገር የሚጠበቅባት ግዴታዎች እና ኃላፊነቶች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመፈናቀል ሁኔታ፣ ኢሰመኮ ለተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ብሔራዊ ሕግ እንዲኖር ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራት እና በረቂቅ ሕግ ዝግጅቱ ወቅት ስለነበረው አስተዋጽዖ፣ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ለማድረግ ብሔራዊ ሕግ ያላቸው ሀገራት ልምድ እንዲሁም ብሔራዊ ሕጉ ከሰብአዊ መብቶች አንጻር የተቃኘ እንዲሆን ከተሳታፊ ተቋማት ምን ይጠበቃል በሚሉት ርዕሶች ላይ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የቀረቡት ጽሑፎች በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ እንዲረዱ እንዳገዛቸው እና ብሔራዊ ረቂቅ ሕጉ ለምክር ቤቱ በሚቀርብበት ጊዜ ለመገምገም የሚረዳቸው ጠቃሚ መረጃ እንዳገኙ ገልጸዋል። በተጨማሪም ጽሑፎቹ በውይይት መድረኩ መገኘት ላልቻሉ የምክር ቤቱ አባላት እንዲደርሳቸው ማድረግ እንደሚገባ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ለማድረግ ብሔራዊ ሕግ መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ኢሰመኮ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ክትትል አድርጎ የለያቸውን ክፍተቶች ለመሙላት የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ የሚመለከታቸው የቋሚ ኮሚቴ አባላት በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በአስፈጻሚ አካላት ላይ ክትትል እንዲያደርጉ ሐሳብ ቀርቧል።
የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ ኢሰመኮ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን የክትትል ግኝቶች መሠረት አድርጎ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ የውትወታ ሥራዎች ሲያከናውን ከምክር ቤቱ አባላት ለተደረገለት ድጋፍ እና ለተገኙ መልካም ውጤቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አክለውም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ለማድረግ የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ በተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ጉልህ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ረቂቅ ሕጉ ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል።