የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከስድስት ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ለተውጣጡ የሕፃናት ምክር ቤት አመራሮች ከጥር 2 እስከ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል። ከምክር ቤቱ አባላትም ጋር ተወያይቷል። በስልጠና እና በውይይት መርኃ ግብሩ ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ እና ከሶማሊ ክልል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የሕፃናት ምክር ቤት አመራሮች ተሳትፈዋል። በዝግጀቱ መጨረሻም አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከሚገኙ አምስት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ዝግጅቱን ተሳትፈዋል።
መርኃ ግብሩ የሕፃናት ምክር ቤቶችን ዐቅም ለመገንባት፣ በኮሚሽኑ የ2015 ዓ.ም. የሴቶች እና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ከባለመብቶች ጋር ለመወያየት እና ከኮሚሽኑ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
በመርኃ ግብሩ የሕፃናት ምክር ቤቶችን ከሚያስተባብረው የክልል ምክር ቤት እና የሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመሆን የሕፃናት ምክር ቤት አመራሮችን ዐቅም ለመገንባት ስለኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር፣ ስለውጤታማ የሕፃናት ተሳትፎ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሕፃናት ተሳትፎ እና የሕፃናት ምክር ቤት ሚናና ተግባር ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በኢሰመኮ የ2015 ዓ.ም. የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት የተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ከኢሰመኮ ከፍተኛ አመራሮችና የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል። በተመሳሳይ በሕፃናት ምክር ቤት አመራሮች የተለዩ መልካም ተሞክሮዎች፣ ተግዳሮቶች እና የማሻሻያ እርምጃዎችን በተመለከተ የሕፃናት ምክር ቤቶችን ከሚያሰተባብሩ የክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም ከክልል ሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የመርኃ ግብሩ አካል በሆነው ተጨማሪ የውይይት መድረክ የኢሰመኮ የ2015 ዓ.ም. የሴቶች እና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ለተለያዩ በሕፃናት መብቶች ላይ ለሚሠሩ ሲቪክ ማኅበራት፣ ለትምህርት ቤቶች ተወካዯች፣ ለወላጆች እና ለሕፃናት ተማሪዎች ሕፃናትን ባሳተፈ መልኩ የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱ ግኝቶች ዙርያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ሪፖርቱ ከጥቃት የመጠበቅ መብትን፤ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሁኔታን፣ ጠለፋና አስገድዶ መድፈርን፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት መብቶች አያያዝን፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የሕፃናት መብቶች አያያዝን፣ በጎዳና ያሉ ሕፃናት መብቶች ሁኔታን፣ በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ የሕፃናት መብቶች ሁኔታን እና የሕፃናት በቂ የኑሮ ደረጃ ማግኘት መብትን የተመለከቱ ጉዳዮችን አካቷል። በዝግጀቱ የሕፃናት መብቶችን የሚዳስሱ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እና የሥዕል ዐውደ ርዕይ ቀርቧል፡፡
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ “የሕፃናት መብቶችን አያያዝ ለማሻሻል በሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች፣ መርሖች እና ዕሴቶች ላይ የተመሠረቱ ምላሾችን በመስጠትና መልካም ተሞክሮዎችን በመተግበር የሕፃናትን ጥቅምና ፍላጎት ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ውጤታማ እና ተጨባጭ መፍትሔን ሊያስገኝ የሚችል የሕፃናት ተሳትፎን ማረጋገጥ የሕፃናት መብቶችን ለማስከበር እና ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።