የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የመገናኛ ብዙኃን የቁጥጥር ሥራዎች ከሴቶች መብቶች አንጻር ያላቸውን አተገባበር በተመለከተ ባከናወነው ጥናት ላይ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይት መድረኩ በጥናቱ የተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ለውይይት የቀረቡ ሲሆን፣ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ አካላት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ በሕግ የመቆጣጠር ሥልጣን በተሰጠው አካል የሚደረግ ቁጥጥር፣ የመገናኛ ብዙኃን የእርስ በእርስ ቁጥጥር እና መገናኛ ብዙኃን በተቋማዊ አሠራራቸው የዘረጓቸው የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓቶች ከሴቶች ሰብአዊ መብቶች አንጻር ያሉባቸው የፖሊሲ፣ የሕግና የአሠራር ክፍተቶች ቀርበዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንን የተመለከቱ ፖሊሲዎችና ሕጎች የሴቶችን ጉዳዮች በሚገባው ጥልቀት በማካተት ረገድ ክፍተቶች ያሉባቸው መሆኑ፤ በብሮድካስት አገልግሎት ተቋማት ላይ ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት የሴቶችን አጀንዳ በተመለከተ በበቂ ሁኔታ መደበኛ ክትትልና ግምገማ የማያደርጉ መሆኑ፤ ከሴቶች መብቶች ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ግምገማዎችና ክትትሎች አብዛኞቹ በወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ተወስነው የሚከናወኑ እንጂ መደበኛ እና ስልታዊ አሠራሮችን አለመከተላቸው እንዲሁም በቂና ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራ አለመኖሩ በጥናቱ የተለዩ ቁልፍ ክፍተቶች መሆናቸው በውይይቱ ተገልጿል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

እነዚህን ግኝቶች መሠረት በማድረግ ኢሰመኮ በጥናቱ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በዝርዝር ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች በመድረኩ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በመገናኛ ብዙኃን ይዘቶችና አሠራሮች የሴቶችን መብቶች በአግባቡ የሚያስተናግድ ውጤታማ የመገናኛ ብዙኃን የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ ወይም ሕግ መቅረጽ እና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ፤ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚዘጋጁ ሌሎች ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ለሴቶች መብቶች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው፤ ተቆጣጣሪ አካላት በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚያደርጉትን ክትትል እና ቁጥጥር በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ባሕርይ ከግምት ባስገባ መልኩ መደበኛ እና ስልታዊ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በጥናቱ መንግሥት ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ይዘቶችና ተቋማዊ አሠራር ሊኖራቸው የሚገባ መብቶች ሊያስተናግድና ውጤት ሊያመጣ የሚችል መገናኛ ብዙኃን የሚመሩበት ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙኃን የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ ወይም ሕግ መቅረጽ እና ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት፣ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚዘጋጁ ሌሎች ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ለሴቶች መብቶች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እና በጥልቀት ሊያካትቱ እንደሚገባ፣ ተቆጣጣሪ አካላት በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚያደርጉትን ክትትል እና ቁጥጥር በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ከግምት ባስገባና ሥልታዊ በሆነ መንገድ ማከናወን ያለባቸው ስለመሆኑ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሚዘጋጁ መመሪያዎች ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የሴቶችን ጉዳይ እንዲያካትቱ በመደበኛነት ሥልት መንደፍ፣ መገምገም እና ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንዳለበት ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረበው ጥናት ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ላይ የተቋሞቻቸውን ሥልጣንና ኃላፊነቶች መሠረት ባደረገ መልኩ የተለያዩ ሐሳቦችን በማጋራት ሰፊ ውይይት አድርገዋል። በተለይም ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን የሚያጋጥሟቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ከግምት ያስገባ ቀጣይነት ያለው ክትትል ማከናወን እንደሚያስፈልግ፤ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ አካላትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች መገናኛ ብዙኃን የሴቶችን መብቶች ባከበረ መንገድ እንዲሠሩ ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎችን ማከናወን እና ለውጤታማነቱም በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መሃል

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ለረዥም ዘመናት የቆየው ያልተመጣጠነ የሥርዓተ ጾታ ግንኙነት አሁንም በተለያየ መልኩ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚንጸባረቅ መሆኑን በመግለጽ፣ “የመገናኛ ብዙኃን የቁጥጥር ሥራዎች ለሴቶች መብቶች መከበር ተገቢውን ትኩረት በሰጠ መልኩ ሊተገበሩ ይገባል” ብለዋል። ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበው፣ ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።