የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሴቶች እና በአካል ጉዳተኞች መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች እና መብቶቹን ለማስጠበቅ የምክር ቤት አባላት ሚና ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም ወቅታዊ በሆኑ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች ላይ ጥር 2 እና 3 ቀን 2016 ዓ.ም. የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡ በመድረኩ ከኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተወካዮች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የአማራ፣ የቤንሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ የሲዳማ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጡ አባላት ተሳትፈዋል።
በውይይት መድረኩ የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ መርሖች እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ አሉታዊ አመለካከቶች የሚወገዱባቸው ስልቶች፤ ኢሰመኮ በ2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ያደረጋቸው የዓመቱ የአካል ጉዳተኞች እና የሴቶች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የሚያሳዩ ሪፖርቶች አንኳር ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል።
ከአካል ጉዳተኞች አንጻር የምክር ቤት አባላት በሕግ አወጣጥ ሂደት ሊጠቀሙበት የሚችሉትን የሰብአዊ መብቶች ማረጋገጫ ዝርዝር ቀርቦ ተሳታፊዎች እንዲወያዩበት የተደረገ ሲሆን፤ ከሕግ ማውጣት፣ ከአፈጻጸም ክትትል እና ቁጥጥር ሥልጣናቸው ጋር በተገናኘ የምክር ቤት አባላት የሴቶችን እና የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ከማስጠበቀ አኳያ ስለአላቸው ሚና ውይይት ተካሂዷል። በተጨማሪም ተሳታፊዎች አካል ጉዳተኞች ከገጠሟቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲማሩ ለማድረግ የግል የሕይወት ተሞክሯቸውን እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን የተለያዩ በሴቶች እና በአካል ጉዳተኞች መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የማኅበራት ተወካዮችም ወቅታዊ እና አሳሳቢ የሚሏቸውን ጉዳዮች አጋርተዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ይህን መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውይይት መድረኮች ለመላው የምክር ቤት አባላት የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕየታዩ ያሉ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ለማስፋፋት የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በተመለከተ ያለውን የግንዛቤ እና የአመለካከት ችግር ለማስተካከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ሐሳብ ሰጥተዋል። የምክር ቤት አባላቱ አክለውም ተወክለው ከመጡባቸው አካባቢዎች አሳሳቢ ናቸው ያሏቸውን የሴቶች መብቶች ጉዳዮችን በማንሳት፤ በሴቶችና ሴት ሕፃናት መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስከትሉ ጎጂ ድርጊቶችን ለማስወገድ የሚሠሩ ሥራዎች የተቀናጁ እና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገቡ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ የሴቶች ሰብአዊ መብቶችን ለማስፋፋትና ለማስከበር እንዲሁም ለጥሰቶች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ኮሚሽኑ በሚሠራቸው ሥራዎች የሕዝብ ተወካዮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። አክለውም የሚወጡ ሕጎች፣ የሕጎቹ የአፈጻጸም እና የክትትል ሂደት የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን ብዝኅ ፍላጎት መሠረት ያደረገና ሙያዊ ዕይታን የተላበሰ መሆን እንዳለበት አሳስባዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ በተለያዩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ከሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች በቀደሚነት እንደሚገኙ እና በልዩ ሁኔታም አካል ጉዳተኛ ሴቶች፣ ሴት አረጋውያን እና አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ካለባቸው ተደራራቢ ተጋላጭነት የተነሳ ከባድ የመብቶች ጥሰት እንደሚደርሱባቸው ገልጸዋል።