የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ-ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ለተውጣጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ለ4 ቀናት የቆየ ስልጠና ከጥቅምት 21 እስከ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አከናውኗል።
ስልጠናው በዋናነት የፖሊስን ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር አቅም ለመገንባት ያለመ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች መሰረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች በተለይም ሰብአዊ ክብር፣ እኩልነት፣ ነጻነት፣ አድሎ አለመፈጸም እና ኃላፊነት ከፖሊስ ተግባር ጋር ያላቸውን ትስስር በተመለከተ የተሳታፊዎችን እውቀትና አመለካከት ለማዳበር የሚያስችሉ ክንውኖችን ያካተተ ነበር፡፡
ተሳታፊዎች ከዋና ዋና የፖሊስ ኃላፊነትና ተግባራት፤ ማለትም ማስቆምና መፈተሽ፣ እስር፣ ምርመራ እና ብርበራ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩና የተያዙ ሰዎች በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች መሰረት ስለተጠበቁላቸው መብቶች ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠናው ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል። በተጨማሪም ስለኃይል አጠቃቀም መርሆች እንዲሁም ስለፖሊስ ተጠያቂነት ያላቸውን እውቀትና አመለካከት ለማዳበር፤ እንደ አመራር ከፖሊስ ሥራና ኃላፊነት በተለይም ከተጠርጣሪዎችና የተያዙ ሰዎች መብቶች ጋር በተያያዘ የሚታዩ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ለመለየት እና ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ስትራቴጂ የመንደፍ ክህሎት በስልጠናው በተግባር እንዲለማመዱ ለማድረግ ተችሏል፡፡
በመጨረሻም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የምርመራ ዘርፍ ኮሚሽነሮች ተገኝተው በስልጠናው ፋይዳ እና ቀጣይነት ላይ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በተጨማሪም ተሳታፊዎች ከዕለት ተዕለት ተግባራቸው ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ርዕሰ-ጉዳዮችን በስልጠናው ያገኙትን እውቀት፣ አመለካከትና ክህሎት በመጠቀም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳሽነት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡