የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል የሚገኙ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት፤ በጦርነቱ ምክንያት የተዳከሙ ማኅበራት ዳግም ሊጠናከሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመለየት እንዲሁም አስቸኳይ እና ዘላቂ መፍትሔ የሚያሻቸውን ጉዳዮች በመለየት ለባለግዴታዎች ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብ ያለመ የውይይት መድረክ ከነሐሴ 10 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ አከናውኗል። በውይይቱ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችን ጨምሮ ከአካል ጉዳተኞች እና ከአረጋውያን ማኅበራት የተወከሉ 50 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በጦርነቱ ወቅት የደረሱ ጉዳቶችን ጨምሮ፣ ግጭቱን ለማቆም ከተደረገው የሰላም ስምምነት ወዲህም የቀጠሉ ችግሮችን አስረድተዋል። በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች እና ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮች በአስቸኳይ ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲደረግ፣ የአካል ድጋፍ እና ተሐድሶ አገልግሎቶች በተጠናከረ ሁኔታ እንዲጀመሩ፣ መድኃኒትን ጨምሮ መሠረታዊ የሕክምና ግብአቶች እንዲሟሉ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ እና የጡረታ አበል ክፍያ ባልተቆራረጠ እና በተሟላ ሁኔታ መፈጸም እንዲጀምር ጠይቀዋል። በተለይም ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው የጡረታ አበል ክፍያው የተጀመረ ቢሆንም እስከአሁን ተሟልቶ ባለመከፈሉ ምክንያት የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ ክፍያን ጨምሮ ለተለያዩ ወጪዎችን ለመሸፈን የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ አለመቻላቸውን አስረድተዋል። አክለውም የአልጋ ቁራኛ የሆኑ እና ከባድ አካል ጉዳት ያለባቸው ጡረተኞች እና አረጋውያን በውክልና እንዲቀበሉ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ ክፍያውን መቀበል አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የአካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ጡረተኞች ማኅበራቱን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ከፋይናንስ ውስንነቶች የተነሳ በሚፈለገው መጠን እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻላቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም ማኅበራቱን ዳግም ለማጠናከርና የተሟላ እንቅስቃሴ ለማስጀመር ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ ኮሚሽኑ በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ መድረኩ በጦርነቱ ወቅት የደረሱ ጉዳቶችን እና ከጦርነቱ በኋላ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚሽነር ርግበ አክለውም፣ እንደ ጦርነት ባሉ አደጋዎች ወቅት አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ለከፉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚዳረጉ እንደመሆኑ፣ ከግጭቶች በኋላ በሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረጋቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።