የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሲቪል ማኅበራት ጋር በትብብር እና በቅንጅት ለመሥራት ያቋቋመው “የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበራት ትብብር መድረክ” የተለያዩ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በኮሚሽኑ ዋና ጽሕፈት ቤት አካሂዷል፡፡
የውይይቱ ዋና ዓላማ የትብብር መድረኩን ለማጠናከርና ወደላቀ ተግባር ለማሸጋገር ይቻል ዘንድ የሥራ እንቅስቃሴውን መገምገም እንዲሁም የትብብር መድረኩን ከኢሰመኮ ጋር የሚመሩ ተባባሪ መሪ (Co-chair) እና የተቋቋሙትን ንዑሳን የትብብር ቡድኖች የሚያስተባብር ምክትል ተባባሪ መሪ (V/Co-chair) የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችን መምረጥ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ ለማሻሻል ከሚከተላቸው ስልቶች መካከል ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጋር በትብብር መሥራት አንዱ በመሆኑ ‘’የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክ” ነሐሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋ መቋቋሙ ተገልጿል፡፡ የትብብር መድረኩ ከተቋቋመ ጀምሮ የተከናወኑ ተግባራትና አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን በቀጣይ የትብብር መድረኩን አጠናክሮ መሄድ አስፈላጊ እንደሆነም ተሰምሮበታል።
ተሳታፊዎች የትብብር መድረኩ ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ መሻሻልና መስፋፋት የሚረዱ ተግባራትን በተሻለ መልኩ እንዲያከናውን የሚያግዙ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ መዋቅራዊ የሰብአዊ መብቶች ተግዳሮቶች እና ጭብጦችን ለመለየት በጋራ የሚሠራበት ምልከታ ላይ ተወያይተዋል። በ2015 ዓ.ም. የተቋቋሙ ንዑሳን የትብብር ቡድኖች ሊጠናከሩ የሚችሉበት ሐሳቦችንም አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም በተሻሻለው የትብብር መድረኩ የጋራ መግባቢያ ሰነድ (TOR) መሠረት የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ለሚቀጥለው 1 ዓመት የትብብር መድረኩ ተባባሪ መሪ እና ምክትል ተባባሪ መሪ ሆነው እንዲያገለግሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች መርጠዋል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የሲቪል ማኅበራት ከኮሚሽኑ ጋር የሚያደርጉት ትብብርና ቅንጅት ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ማሻሻልና ማስፋፋት ሥራ ትልቅ አንድምታ እንዳለው ገልጸዋል። ለትብብር መድረኩ ውጤታማነትም የሁሉም አባል ሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ እና ቁርጠኛ የሆኑ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እንደሚያስፈልጉ አስገንዝበዋል።