የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽኑ ከኅዳር 28 እስከ ታኅሣሥ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በአምስት ዞኖች በሚገኙ 22 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባደረገው ክትትል ግኝቶች ላይ የተመሰረተው ይህ ውይይት፣ በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የታዩ ጥንካሬዎችና ክፍተቶች ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ተቀብሏል። በተለይም ሕግን ያልተከተለ እስር፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር፣ ከምግብ፣ ውሃ እና የሕክምና አገልግሎት ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮች፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለማክበር፣ እንዲሁም የመቆያ ክፍሎች እጥረት፣ ኢሰብዓዊ አያየዝ፣ ልዩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ተጠርጣሪዎች መደረግ ስላለበት ድጋፍ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ተነስተው ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በጅማ ከተማ በተደረገው ውይይት ከምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ኢሉ አባቦር፣ ቡኖ በደሌ እና ጅማ ዞን እና የወረዳ የፖሊሰ ጣቢያ አመራሮች፣ በጨፌ ኦሮሚያ ከአስተዳደር፣ ሕግ እና የሰው ኃይል ልማት ቋሚ ኮሚቴ እና ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ የተወጣጡ 36 አመራሮች ተሳትፈዋል። 

የክትትሉን ግኝቶች ለተሳታፊዎች ያቀረቡት የኢሰመኮ የጅማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ “ውይይቱ በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶችን በማረም የተሻለ የተጠርጣሪዎች አያያዝ ለመፍጠር ከኢሰመኮ ጋር ለመስራት መግባባት ላይ ለመድረስ ያስቻለ ነው” ብለዋል። ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው በክልሉ የተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የታዩ ክፍተቶች እንዲሻሻሉ ከኢሰመኮ ጋር በቅርበት ተባብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በተመሳሳይ መልኩ ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በጅማ ከተማ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ኢሉ አባቦር፣ ቡኖ በደሌ እና ጅማ ዞን ማረሚያ ቤቶች አመራሮች፣ ከክልሉ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ኮሚሽን፣ በጨፌ ኦሮሚያ ከአስተዳደር፣ ሕግ እና የሰው ኃይል ልማት ቋሚ ኮሚቴ እና ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ከተወጣጡ 25 ኃላፊዎች ጋር በታራሚዎችና በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች አያያዝ ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡ 

ይህ ውይይት ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 12 እስከ ታኅሣሥ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በስድስት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 10 ማረሚያ ቤቶች ላይ ባደረገው የክትትል ግኝቶች ላይ የተመሰረተ ነበር። በክትትሉ በማረሚያ ቤቶች ከታራሚ አያያዝ አንጻር አጅግ አበረታች ለውጦች መኖራቸው ተመልክቶ፣ በተለይም በክልሉ የታራሚ የይቅርታ አሰጣጥ መቆሙ፣ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው እስረኞች የቅጣት አፈጻጸም ላይ የታዩ ክፍተቶች፣ የማረሚያ ቤቶች የታራሚ መረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ የተደፈ አለመሆን፣ ከሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያያዘው ያለው ችግር ሳይቀረፍ መቀጠሉ፣ በማረሚያ ቤቶች ልዩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ታራሚዎች ተመጣጣኝ ማመቻቸት አለመኖሩ ውይይት ተደርጎባቸው በቀጣይ መሰራት የሚገባቸው ስራዎች ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች የምርመራና ክትትል ስራ ክፍል ሪጅናል ዳይሬከተር አቶ ኢማድ አብዱልፈታህ “በማረሚያ ቤቶች የታየው ለውጥ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው በክትትሉ የተለዩና  የከፍተኛ አመራር ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ተገቢ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል” ብለዋል።