የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2017 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በሐረሪ ክልል በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በ2016 ዓ.ም. በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ ከሰኔ 21 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በድሬዳዋ እና በሐረር ከተሞች ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ከድሬዳዋ ፖሊስ እና ማረሚያ ቤት፣ ከከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት፣ ከፍትሕና ሕግ ጉዳዮች ቢሮ፣ ከሴቶችና ሕፃናት ቢሮ፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር ድሬዳዋ ቅርንጫፍ፣ ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት እና ከጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ እንዲሁም ከሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤት አስተዳደር ኮሚሽን፣ ከማረሚያ ቤት አስተዳደር፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና በሥሩ ከሚገኙ 11 ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ከፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት፣ ከምክር ቤት፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ፣ ከጤና ቢሮ እና ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ ተወካዮች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ በክትትል ሪፖርት የተለዩ ግኝቶች የቀረቡ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን በፈርጅ ለይቶ መያዙ፣ የቀለም ትምህርት መሰጠቱ፣ ድብደባ እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ መቀነሱ፣ የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ መቀረቡ፣ የጤና አገልግሎት መሰጠቱ፣ ታራሚዎችን በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ መቀበላቸው፣ የማረሚያ ቤቶች ግቢ እና የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች ንጽሕና እና የውሃ አቅርቦት መሻሻሉ በአበረታችነት ተገልጸዋል። በተመሳሳይ በፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች በሕግ በተቀመጠ ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸው እና የፍርድ ቤት ትእዛዝ መከበሩ፣ የተራዘመ ቅድመ ክስ እስራትን ለማስቀረት ልዩ ትኩረት መሰጠቱ እና ሥልታዊ የሆነ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ አለመኖሩ በመልካም አፈጻጸም መለየታቸው ተመላክቷል።

በሌላ በኩል ማረሚያ ቤቶቹ ለሴት ታራሚዎች የሚሰጡት የትምህርትና የሙያ ስልጠና እንዲሁም የሥራ ዕድል አነስተኛ መሆኑ፣ ለሴቶች የተመቻቸ የአምልኮ ስፍራ አለመኖሩ፣ ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚቆዩ ሕፃናትን በሚመለከት ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እና የአሠራር ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ ለአእምሮ ሕሙማን እና ለአካል ጉዳተኛ ታራሚዎች ልዩ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ ድጋፍ አለመኖሩ እንዲሁም የምግብ አቅርቦት መጠን እና ጥራት ላይ ያለ ክፍተት መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተነስቷል። በፖሊስ ጣቢያዎችም የተጠርጣሪዎች ማቆያ ክፍሎች የተጨናነቁ መሆናቸው፣ የምግብ፣ የግል እና የጋራ ንጽሕና መጠብቂያ አቅርቦቶች ውስን መሆናቸው እና አልፎ አልፎ በፖሊስ አባላት ድብደባ የሚፈጸም መሆኑ የማስተካከያ እርምጃዎች የሚያስፈልጋቸው ግኝቶች መሆናቸው ተገልጿል

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች መሠረት በማድረግ የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰው፤ በቀረበው ሪፖርት የተለዩ ግኝቶችን ለማረም እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ለመተግበር እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራው የለያቸው ግኝቶችን እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ለመፈጸም የሚያስችል የድርጊት መርኃ ግብር በተሳታፊዎች ተዘጋጅቷል።
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር በዳሳ ለሜሳ በክልሉ የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ አበረታች ለውጦች የሚስተዋሉ መሆኑን ገልጸው፣ ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲከበሩ ባለድርሻ አካላት ስላላቸው ሚናና የቅንጅት ሥራ አብራርተዋል። አክለውም በባለድርሻ አካላት የተዘጋጀው የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም የድርጊት መርኃ ግብር በአግባቡ ሊተገበር እንደሚገባ አሳስበው ኢሰመኮ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።