የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 15 እስከ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል በሚገኙ 4 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እና አዲስ ጥገኝነት ጠያቂዎች በሚገኙባቸው ሁለት ስፍራዎች፤ እንዲሁም ከጥቅምት 5 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. በሁለት የጥገኝነት ጠያቂዎች መቀበያ ስፍራዎች በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ክትትል እና ምርመራ በማድረግ በለያቸው ግኝቶች ላይ ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል። 

በውይይቱ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት፣ የትምህርት ቢሮ፣ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የኑዌር ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ የተ.መ.ድ. የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ( United Nations High Commissioner for Refugees (UNHCR))፣ የስደተኞች እንዲሁም የሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱ ኢሰመኮ በክልሉ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች በሚገኙ ስደተኞች እና በተለያዩ መቀበያ/ማቆያ ስፍራዎች በሚገኙ አዲስ የደቡብ ሱዳን ዜግነት ያላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ባከናወነው ክትትል እና ምርመራ የለያቸው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። ከለጋሽ ሀገራት የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ ጋር በተያያዘ ለስደተኞች የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ እና ጥበቃ እየቀነሰ መምጣቱ፤ ስደተኞች ኑሯቸውን ለመደጎም አሉታዊ ውጤት በሚያስከትሉ የሥራ ዘርፎች በመሰማራታቸው በተለይም ለጉልበት ብዝበዛ እና ለጥቃት መጋለጣቸው፤ ለዚህም ተገቢውን ፍትሕ እያገኙ አለመሆኑ፤ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚ እና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት መቋረጣቸው፤ ጦርነት ሸሽተው አዲስ እየገቡ ላሉ የደቡብ ሱዳን ጥገኝነት ጠያቂዎች ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የልየታ እና ምዝገባ ሥራ የተጀመረ ቢሆንም በመቀበያ ስፍራዎች በቂ የአደጋ ጊዜ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑ እንዲሁም ስደተኞች ከድጋፍ በመላቀቅ ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ አስቻይ ሁኔታ አለመፈጠሩ ተገልጿል። በተጨማሪም ስደተኞች በችግር ምክንያት ከመጠለያ ጣቢያ ውጪ የማገዶ እንጨት እና የጫካ ጎመን ለመልቀም እንዲሁም ውሃ ለመቅዳት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ግድያን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚፈጸምባቸው እና ለዚህም ተገቢውን ፍትሕ እንደማያገኙ ተነስቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በኮሚሽኑ የቀረቡት ግኝቶች ወቅታዊና ሁኔታውን የሚያሳዩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ በዓለም አቀፍ ደረጃ የለጋሽ ሀገራት ድጋፍ መቀነስ፣ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት እና በሰብአዊ ድጋፍ ብቻ ላይ ጥገኛ መሆን ለስደተኞች የሚደረገውን ጥበቃ እና ድጋፍ አስቸጋሪ እያደረገው መምጣቱን ገልጸዋል። በተለይም ከድንገተኛ ምላሽ ውጭ ያሉ ዘላቂ መፍትሔዎች፤ ለተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ ልዩ ድጋፍ፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፤ የማኅበራዊ ትስስር፤ ለጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች እና ሌሎች የፍትሕ አገልግሎቶች በበጀት እጥረት ምክንያት በመቋረጣቸው ስደተኞች አስቸጋሪ ሕይወት እየገፉ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። ለዚህም አገር በቀል አማራጮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በሌላ በኩል አዲስ እየገቡ ላሉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ድጋፍ እና ጥበቃ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነገር ግን በበጀት እጥረት፤ በደኅንነት ስጋት እና አካባቢውን ባጥለቀለቀው ጎርፍ ምክንያት የሚፈለገውን ያክል ሥራ አለመሠራቱን በማንሳት በኮሚሽኑ የተለዩ ግኝቶችን እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተቀብለው ወደፊት ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠሩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የስደተኞች እና የፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ምሕረተአብ ገብረመስቀል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበትን የጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ እና የስደተኞችን ጸጥታና ደኅንነት ማረጋገጥ ሂደት የታዩ ክፍተቶችን መቅረፍ እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም ዳይሬክተሩ በክትትል እና ምርመራ ሥራው የተለዩ ችግሮችን በመፍታት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲከበሩ ባለድርሻ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።