የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ኅዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኢሰመኮ በክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው ክትትሎችና ምርመራዎች የደረሰባቸውን ግኝቶች በማቅረብ መልካም እመርታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በአሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለመወትወት ያለመ ነው። በውይይቱ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ዓለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የሰላምና ጸጥታ፣ የፖሊስ ኮሚሽንና የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።






በመድረኩ ኢሰመኮ በክልሉ ባደረጋቸው ክትትሎችና ምርመራዎች የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች በቤተሰብ አባላት እንዲሁም በሕግናና በሃይማኖት አማካሪዎች በመጎብኘት መብታቸው ላይ ምንም ዐይነት ክልከላ የማይደረግባቸው መሆኑ፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች አዳዲስ የማቆያ ክፍሎች፣ ቢሮዎችና መጸዳጃ ቤቶች መገንባታቸው፣ በማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ማረሚያ ቤት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መጀመሩ፣ ያለአግባብ ታስረው የነበሩ ከ50 በላይ ሰዎች መለቀቃቸው፣ ተጠርጣሪዎች ሲያዙ የተያዙበት ምክንያት የሚገለጽላቸውና የፍርድ ቤት ትእዛዝ የሚከበር መሆኑ፣ ታራሚዎች በሚረዱት ቋንቋ አገልግሎት እንዲያገኙ አስተርጓሚዎች መመደባቸው እንዲሁም የታራሚዎች የቀን የነፍስ ወከፍ የቀለብ በጀት ከነበረበት 41 ብር ወደ 75 ብር መሻሻሉ አበረታች መሆኑ ተጠቅሷል።






በሌላ በኩል ሁሉም ማረሚያ ቤቶች ምግብ የማያቀርቡ መሆኑና በምትኩ የሚሰጠው 75 ብር ምንም እንኳን ከቀድሞው አንጻር የተሻለ ቢሆንም አሁን ካለው የገበያ ዋጋ ጋር ስለማይመጣጠን ታራሚዎችን ለችግር መዳረጉ፤ የማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁና ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው እንዲሁም ለመኝታ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች የሌሏቸው መሆኑ፤ የመጸዳጃ ቤቶች የንጽሕና ጉድለት፣ የመጠጥ እና ንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት አለመሟላት፣ በቂ የሕክምና አገልግሎት አለመኖር፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች አልፎ አልፎ የሚፈጸም ድብደባና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ፤ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ የሆኑ ተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎችን ሁኔታ ያገናዘበ አያያዝ አለማድረግ እንዲሁም የፍትሕ ሂደት መጓተትና ሕገ ወጥ እስራት በክልሉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ዓለሚቱ ኡሞድ ኢሰመኮ በዝርዝር ያነሳቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በበጎ እንደሚመለከቷቸው ገልጸው በጥንካሬ የቀረቡትን በማስቀጠል እንዲሁም ሊስተካከሉ የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች መሠረት ክልሉ በዕቅድ በማካተት ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠራ ገልጸዋል። አክለውም ከድንበር ዘለል ጥቃቶች እና ከስደተኞች መብቶች አተገባበር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት የፌዴራል መንግሥት በልዩ ትኩረት ክልሉን እንዲያግዝ ኢሰመኮ የውትወታ ሥራዎችን እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በክልሉ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ጠንካራ የቅድመ መከላከል ሥራ እንዲሠራ፤ የስደተኞች፣ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንዲሁም የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሁኔታ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ፈጻሚዎችን በመለየት ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራዎች እንዲከናወኑ፤ በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻል ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፤ ተጠርጣሪዎች ለተራዘመ እስራት የሚዳረጉበት ሁኔታ እንዲታረም እንዲሁም የተጠርጣሪዎችና የተከሰሱ ሰዎች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር እና ክልሉ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደአስፈላጊነቱ እና አግባብነቱ የፌዴራል መንግሥት እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም ኢሰመኮ በክልሉ የሚያከናውናቸውን የሰብአዊ መብቶች ስልጠና፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የክትትል፣ የምርመራና የውትወታ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።