የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የጋምቤላ ክልል አካባቢዎች ሲከሰቱ የቆዩ የትጥቅ ግጭቶችን፣ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶችንና አጠቃላይ የጸጥታ ችግሮችን እና በዚህ ሳቢያ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ተጎጂዎችን፣ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች እንዲሁም የክልሉን የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎችን በማነጋገር ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል።
በተለይም ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ላለው የጸጥታ ችግር መነሻ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተወሰኑ ነዋሪዎች መካከል የተነሳ አለመግባባት መሆኑ ማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ይሄው አለመግባባት በፍጥነት ወደ ብሔርን መሠረት ያደረገ ውጥረት እንደተሸጋገረ ነዋሪዎች ያስረዳሉ። ይህንኑም ተከትሎ የተለያየ ብሔር ታጠቂ ቡድኖች በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግ ወረዳ፣ በጋምቤላ ከተማ ብሔር ብሔረሰቦች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እና በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሰፈሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት በርካታ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ደርሷል። በጸጥታው ችግር ምክንያት ገና ወደ አካባቢዎቹ በአካል ደርሶ ምርመራ ለማድረግ ያልተቻለ ቢሆንም፣ ነዋሪዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ መንደሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የወደሙ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን በሚመጡ ታጣቂ ቡድኖች በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ በክልሉ በሚኖሩ ብሔሮች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ክልሉ ወደ 350 ሺህ የሚጠጉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን በስምንት የተለያዩ ካምፖች ያስተናግዳል።
ከሁለት ወራት በላይ ለዘለቀው የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ችግር እና በክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በመድረስ ላይ ያሉ ግጭቶች ተሳታፊዎችን በተመለከተ ተጎጂዎችም ሆነ የክልሉ የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎች የተለያዩ ብሔር ታጣቂ ቡድኖችን ኃላፊነት ይጠቅሳሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች የክልሉ ኑዌር ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ በሌላ አካባቢ የአኝዋ ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች እና በአንዳንድ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ እንደሚኖሩ የተገለጸ ሰዎች ጭምር በግጭቶቹ ተሳታፊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ጥቃቶች እና ግጭቶች በአብዛኛው ብሔር ተኮር ሲሆኑ በሌላ በኩል ግጭት የሚደርስባቸውን አካባቢዎች ያለ የብሔር ልዩነት ሁሉንም ነዋሪዎች አካባቢውን ሸሽቶ ለመፈናቀል፣ ለንብረት ውድመት እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ያጋለጠ ነው። በሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ቀደም ብሎ ባሉት ቀናቶች በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ነዋሪዎች በደረሰባቸው ሥጋት ሳቢያ የጋምቤላ ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴ ቀንሶ፣ ብሎም ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ከሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰኑ ቀናት ተግባራዊ የሚሆን ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እስከ ጠዋት 12፡00 ሰዓት የሚዘልቅ እና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተፈጻሚ የሚሆን የሰዓት እላፊ ገደብ፣ እንዲሁም ከተመደቡ የጸጥታ አካላት ውጪ መሣሪያ ይዞ የመንቀሳቀስ ገደብ ጥሏል።
በተጨማሪም የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተውጣጣ ኃይል ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ ተሰማርቷል። ይህም የክልሉን ጸጥታ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ያረጋጋው ሲሆን፣ በጋምቤላ ከተማ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲጀመር አስችሏል።
ሆኖም በክልሉ የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ አፈጻጸም ነዋሪዎችን ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይዳርግ መከላከልን ጨምሮ፣ በክልሉ በተለያየ ወቅት የሚያገረሹ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረጉ ጥቃቶችን እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ተጨማሪ ትኩረት እና ክትትል ማድረግ ይገባል። ስለሆነም በክልሉ የተሰማራውን ከፌዴራል እና ከክልሉ የጸጥታ አካላት የተውጣጣ ኃይል ማጠናከር እና አስፈላጊውን ድጋፍ ከመስጠት ተግባር ጎን ለጎን፣ ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ በደረሰው ግጭት ሳቢያ አከባቢውን ለቀው ለሸሹ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ ማድረስ፣ በግጭቱ የተነሳ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል። እንዲሁም ለረጅም ዓመታት እና በየጊዜው ወደ ግጭት ለሚያመራው በተቀባይ ማኅበረሰብ እና በስደተኞች መካከል ላለው የላላ ግንኙነት ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ያስፈልጋል::
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህንኑ ተግባር ለመደገፍ እና በተለይም በነዋሪዎች እና በክልሉ በተጠለሉ ስደተኛ ካምፖች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ከነዋሪዎች፣ ከስደተኞች ተወካዮች፣ ከተቀባይ ማኀበረሰብ ተወካዮች፣ ከፌዴራል እና ጋምቤላ ክልል ጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም በስደተኞች አያያዝ ላይ ከሚሠሩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የተውጣጣ ጊዜያዊ አስተባባሪ የሥራ ቡድን ማዋቀር ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው” መሆኑን ገልጸው፣ ኢሰመኮ በማድረግ ላይ የሚገኘው ክትትል የሚቀጥል ነው ብለዋል።