የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች፤ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ሌሎች ይፋዊ ያልሆኑ ማቆያ ስፍራዎች ላይ በ2015 ዓ.ም. ባከናወነው የታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና አጠባበቅ ክትትል ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚዛን ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ የጋምቤላ ክልል ማረሚያ ቤት አስተዳደር ኀላፊዎች፤ የፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ ኀላፊ፤ የፖሊስ ጣቢያ አዛዦች እና መርማሪ ፖሊሶች እንዲሁም በክልል እና በዞን ደረጃ የሚገኙ የተለያዩ የፍትሕ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ኮሚሽኑ ባከናወነው ክትትል በማረሚያ ቤቶች፤ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በሌሎች ይፋዊ ያልሆኑ ማቆያ ስፍራዎች የታዩ እምርታዎችን ለማበረታታት እንዲሁም የተለዩ ክፍተቶችን፣ አሳሳቢ ጉዳዮችን እና ወደፊት ሊወሰዱ የሚገባቸው የማስተካከያ እርምጃዎችን በተመለከተ ምክክር ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በውይይት መድረኩ በተጠርጣሪ ማቆያ ስፍራዎች እና በማረሚያ ቤቶች ላይ ያተኮሩ ሁለት የክትትል ሪፖርቶች ቀርበዋል። በተጠርጣሪዎች እና በታራሚዎች ላይ የሚደረግ ፍተሻ እና ብርበራ በሕግ አግባብ የሚከናወን መሆኑ፣ ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች ከቤተሰቦቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘት መብት መከበሩ የክትትል ሪፖርቶቹ ከጠቀሷቸው እመርታዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ለታራሚዎች የሚከፈለው የቀን ቀለብ መጠን ከአምናው መሻሻል ማሳየቱ፣ የእምነት ነጻነት መብት ላይ ገደብ አለመኖሩ እንዲሁም በማጃንግ ዞን እና ጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤቶች ለታራሚዎች ገቢ ማስገኛ ሥራዎች መኖራቸው እና በኢታንግ ልዩ ወረዳ፤ ጋምቤላ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማጃንግ ዞን ማረሚያ ቤት ተጨማሪ የተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች ግንባታ መጀመራቸው እንደዚሁ በመልካም ሁኔታ የተለዩ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በክትትሉ ከተለዩና በውይይቱ ከተነሱ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች የዘፈቀደ እስር እና በፖሊስ አባላት የሚፈጸም ድብደባ መኖሩ፣ በአብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በ 48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የማይቀርቡ መሆናቸው እና በተራዘመ የጊዜ ቀጠሮ ምክንያት የፍትሕ መጓተት መኖሩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ሕክምናን ጨምሮ በመንግሥት የሚቀርቡ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ያልተሟላላቸው መሆናቸው፣ የማደሪያ ክፍሎች በቂ አለመሆን፣ የቅሬታ ማስተናገጃ እና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመኖር፣ የበጀትና ቁሳቁስ እጥረት ያለባቸውና ምቹ የሥራ ከባቢ የሌላቸው መሆናቸው እንዲሁም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ የተለየ ድጋፍና ጥበቃ አለመኖሩ በክፍተት ከተለዩ ግኝቶች መካከል ይገኙበታል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ከፍተኛ የሆነ የበጀት እና ሎጀስቲክ እጥረት በሥራቸው ላይ ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን እንዲሁም አብዛኛው የፖሊስ አባላት በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ለረጅም ዓመታት ምንም ዐይነት ስልጠና አለመውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ተጠርጣሪዎች ለረጅም ጊዜ ፍትሕ ሳያገኙ የሚቆዩበት ምክንያት የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ተገቢ ትኩረት ባለመሰጠታቸው እና አልፎ አልፎ በሚኖር የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ ሩት በኮሚሽኑ የክትትል ሥራ የተለዩ ክፍተቶችን እና አሳሳቢ ጉዳዮችን የሚመለከታቸው የፖሊስ ጣቢያ ጽሕፈት ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች ተቀብለው ማስተካከያ እንዲያደርጉ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት፤ ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤት አስተዳደሮች የታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ እንዲሻሻል በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡