የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) 5ኛውን ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (5th National High Schools Human Rights Moot Court Competition) ፍጻሜ ውድድር ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። ከሚያዚያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ በቆየው ውድድር በ12 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ 90 ትምህርት ቤቶች 180 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
በክልሎች በተካሄዱ የማጣሪያ ውድድሮች ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ 8 ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት ከግንቦት 17 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደው ሀገር አቀፍ የቃል ክርክር ውድድር በሩብ እና በግማሽ ፍጻሜ ዙሮች ሲሳተፉ ቆይተው በዛሬው ዕለት የፍጻሜ ውድድር አድርገዋል። በግማሽና በሩብ ፍጻሜ የተወዳደሩ ትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች፡-
- ከቢሾፍቱ ከተማ የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ (ተማሪ ሲፈን ደረጄ እና ተማሪ ሚልኬሳ ንጋቱ)፣
- ከደሴ ከተማ የይሁኔ ወልዱ መታሰብያ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት (ተማሪ ሀውለት ረመዳን እና ተማሪ በረከት ጸጋ)፣
- ከድሬዳዋ ከተማ አዲስ ሕይወት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ኢማን ጀማል እና ተማሪ ዛኪር ዘይኑ)፣
- ከዲላ ከተማ ዲላ ደምቦስኮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ የዓለም ሲሳይ እና ተማሪ መልካም አስራት)፣
- ከሐረር ከተማ ሐረር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ሀምዛ ሙሳ እና ተማሪ አያንቱ ደረጀ)፣
- ከመቀለ ከተማ ቓላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ሣራ አፅብሀ እና ተማሪ አትክልቲ አብረሃ)፣
- ከሚዛን ከተማ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ እዮብ ከፍያለው እና ተማሪ ሃና ጥበቡ) እና
- ከወልቂጤ ከተማ ያበሩስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ተማሪ ሃናን መዚድ እና ተማሪ እዮብ ሚካኤል) ናቸው።
ለፍጻሜ ውድድሩ የደረሱት ተወዳዳሪ ተማሪዎች ከኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ የመጡት ተማሪ ሲፈን ደረጄ እና ተማሪ ሚልኬሳ ንጋቱ፤ እንዲሁም ከይሁኔ ወልዱ መታሰብያ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ ሀውለት ረመዳን እና ተማሪ በረከት ጸጋ ሲሆኑ የቃል ክርክራቸውን በምስለ-ችሎቱ ግራና ቀኝ ቆመው አመልካችና ተጠሪን ወክለው አካሂደዋል።
በዚሁ መሠረት ተማሪ ሲፈን ደረጄ እና ተማሪ ሚልኬሳ ንጋቱ ከቢሾፍቱ ከተማ የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ የፍጻሜ ውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል። በተጨማሪም የውድድሩ ምርጥ የቃል ተከራካሪ በመሆን ተማሪ ሲፈን ደረጄ ከኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ ያሸነፈች ሲሆን በምርጥ የጽሑፍ ክርክር ደግሞ በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ልማት ማኅበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ቢሾፍቱ ቅርንጫፍ የመጡት ተማሪ ሲፈን ደረጄ እና ተማሪ ሚልኬሳ ንጋቱ አሸናፊዎች ሆነዋል።
የዘንድሮው ውድድር ምናባዊ ጉዳይ ከልማት ተነሺነት ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች መርሖዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና አሕጉራዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎችን በማንሳት ተወዳዳሪ ተማሪዎች ጥናት እንዲያደርጉ እና ዕውቀት እንዲያካብቱ አጋጣሚን ፈጥሯል።
የምስለ-ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የተዳኘ እና የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የተከተለ አስተማሪ የውድድር ዐይነት ነው። ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተመሥርተው አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር ያደርጉበትም ጭምር ነው።
በፍጻሜ ውድድሩ ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ተወካዮች፣ መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የተለያዩ ሀገራት ኢምባሲዎች ተወካዮች፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች የሚከበርበት ባህልን ለማጎልበት ተተኪ ትውልድን በመደበኛው ትምህርት ቤት በሰብአዊ መብቶች ዕውቀትና ክህሎት ማነጽ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም ይህንንም ለመተግበር ከሚያስችሉ ሥልቶች መካከል የተማሪዎች ምስለ-ችሎት ውድድር አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።