የኢትዮጲያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኅዳር 15 እና 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚካሄድና መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ስብሰባ የኮሚሽኑን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ በይፋ አስተዋውቋል። ለባለፉት በርካታ ወራት ሰፊ አካታች ሂደት ሲዘጋጅ የቆየው ይህ የስትራቴጂ እቅድ ኮሚሽኑ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ሊሰሩና ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብሎ የለያቸው ቁልፍ የውጤት መስኮችንና ዋና ዋና ተግባራትን አካቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የስትራቴጂ እቅዱን አዘገጃጀት ሂደት አስመልክቶ “የኮሚሽኑን ሰራተኞችና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር፣ እንዲሁም ነባራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል” ብለዋል። የስትራቴጂ ዕቅድ ዝግጅቱ የመጨረሻ ውጤት በኮሚሽኑ አመራር እና በሁሉም ሰራተኞች ዘንድ በባለቤትነት እንዲያዝ ብሎም በስኬት የመተግበሩን ዕድል በሚጨምር መልኩ አሳታፊ እና ምክክርን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የተከናወነ ነው፡፡
“ይህ የስትራቴጂ ዕቅድ ኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት መሰረት የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንዲመራ፤ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት (2014-2018) ካሉት እና ወደፊት ሊከሰቱ ይችላሉ ከሚባሉ ብሔራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታዎች አንጻር ስልታዊ/ስትራቴጂያዊ ትኩረት እንዲኖረው ለማስቻል ታልሞ” መዘጋጀቱን የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ አስረድተዋል።
የስትራቴጂ እቅዱ ዋና ዋና ይዘቶች በኅዳር 15 እና 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በተዘጋጀው ስብስባ ለተሳተፉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማትና የኢሰመኮ አጋር ድርጅቶች ቀርበዋል። በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የሚሰራ በመሆኑ በአዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ በተጨማሪ በአሶሳ፣ በባሕርዳር፣ በጋምቤላ፣ በሀዋሳ፣ በጅማ፣ በጅግጅጋ፣ በመቀሌ እና በሰመራ ከተሞች ስምንት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች እንዳሉትና ስትራቴጂክ እቅዱን ለማስፈጸም የሚያስችለው አዲስ መዋቅር ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉ ተገልጿል።
ስለሆነም የኮሚሽኑ ዓላማ ፈጻሚ የስራ ክፍሎች የሰብአዊ መብቶች ትምህርት፣ የሰብአዊ መብቶች ምርመራና ክትትል፣ የሴቶችና ሕጻናት መብቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች፣ የስደተኞች የተፈናቃዮችና ፍልሰተኞች መብቶች፣ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች፣ እና የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የዋና ኮሚሽነሩን ጽ/ቤት ጨምሮ በሕግና ፖሊሲ፣ በሚዲያና ኮሚሙኒኬሽን፣ በእቅድና አጋርነት፣ በሰው ሃብት፣ በፋይናንስና አስተዳደር፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ድጋፍ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች እንዳሉት ተነግሯል።
የኮሚሽኑ ስትራቴጂክ እቅድ የኮሚሽኑን ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ እሴቶች እና መርሆዎች መሰረት በማድረግ፣ የኮሚሽኑን ስትራቴጂካዊ ተቀዳሚ ተግባራት (Strategic Priorities) ለይቷል። የኢሰመኮ ራዕይ “ሰብአዊ መብቶች ባሕል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ገለልተኝነት፣ አካታችነት፣ አጋርነት እና ለተጎጂዎች/ለጉዳት ተጋላጭ ከሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጎን መቆም በሚሉ ዋና ዋና እሴቶች የሚመራ ይሆናል።
ስትራቴጂክ እቅዱ ያስቀመጣቸው አምስት ቁልፍ የውጤት መስኮች መሰረት ያደረገ ዝርዝር የአፈጻጸም መርኃ ግብሮች ተዘርዝረዋል። እነሱም፡
- በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እንዲኖር ማስቻል፣
- የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራን በማጐልበት ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅ አይነተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ፣
- የቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የዘርፍ ጉዳዮች ውጤታማ የሆነና የሁሉም የሰብአዊ መብቶች ዘርፎችን መስፋፋት፣ መከበርና እና ጥበቃ እንዲኖር ማስቻል፣
- ኮሚሽኑ ተግባርና ኃላፊነቱን የሚያሳካ ተቋማዊ አቅም እንዲኖረው የሰው ሃብት፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን አቅምና ስልቶች ጨምሮ ዘርፈ ብዙ የተቋም አቅም ግንባታ ስራዎች ማከናወን ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ተቋማዊ አሰራሩ አካታች (inclusive) መሆኑን ለማረጋገጥም በሁሉም የኮሚሽኑ ተግባሮችና አገልግሎቶች ውስጥ ሥርዓተ ፆታ፣ የአካል ጉዳተኝነት መብቶችንና የብዝሃነት መርሆች መካተቱን ማረጋገጥ፣
- እንዲሁም አጋርነትን (Partnership) በተመለከተ ኮሚሽኑ ዓላማውን ለማስፈጸም ይረዳው ዘንድ ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት እና የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን ጨምሮ ተባብሮ መስራት መሆናቸውን ተገልጿል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀው መድረክ “ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መስፋፋት ጠቃሚና አካታች የሆኑ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ ከድሮው በበለጠ አብሮ ለመስራት መንገዶች የሚከፈቱበት መድረክ እንደሚሆን” ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል፡፡