የካቲት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ደራሲያን፣ ፊልም ዳይሬክተሮች፣ የኪነጥበብና የሥነ ጥበብ ዘርፍ መምኅራን፣ የዜማና የግጥም ደራሲያን እንዲሁም የተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶች አስተባባሪዎችና የማኅበራት ተወካዮች የተገኙበትን እና በኢሰመኮ ዋና መስሪያ ቤት የተካሄደውን ይህን ስብሰባ ዓላማ ሲያስረዱ፣ የአጋርነት ስራ ክፍል ዳይሬክተር ሃና አንዳርጋቸው “በዋነኛነት የኪነጥበብ ቡድኑን አስፈላጊነት ማስተዋወቅና ባለሞያዎች ከኮሚሽኑ ጋር ለመስራት የሚያስችላቸውን ማዕቀፍ ለመዘርጋት የሚያስችል ግብዓት ለመቀበል” መሆኑን ገልጸዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ኪነጥበብና ሥነ ጥበብ በባሕሪው ስለ መልካም ሥነ ምግባር እና ስለሰብአዊነት በማስተማር ረገድ የሚጫወተውን ሚና አስታውሰው፣ ኮሚሽኑም ይህንን ተገንዝቦ ሁሉንም የኪነጥበብ ዘርፎች ያካተተ የአማካሪ ቡድን ለማቋቋም እንደወሰነ አስረድተዋል። በተጨማሪም ኅዳር ወር 2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ መልኩ ከበርካታ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ጋር ባደረገው ውይይት ባለሞያዎቹ ኮሚሽኑን በበለጠ ሊያግዙ የሚችሉበት ይፋዊ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ መወሰኑና፣ በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. በኢሰመኮ አዘጋጅነት የተካሄደው የመጀመሪያው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫልም የዚህ ትብብር አንዱ ውጤት መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የመጀመሪያ ዙር ውይይት ኢሰመኮ ለዚሁ ዓላማ ያሰበውን የኪነ ጥበብ እና የሥነ ጥበብ አማካሪ ቡድን ኃላፊነትና ተግባራት የሚገልጽ ረቂቅ ቢጋር (Terms of Reference) ላይ ተወያይቷል። ስብሰባውን የተካፈሉት ባለሞያዎች ኮሚሽኑ ያለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የኪነጥበብ እና የሥነ ጥበብ ባለሞያዎችን ለማሳተፍ ማቀዱ ተገቢና የሚመሰገን እንደሆነና በዚህ ውይይት የተጀመረውን ሂደት እንደሚደግፉት ገልጸው፣ በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ በርካታ ገንቢ አስተያየቶች ሰጥተዋል።