የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሀገር ውስጥ በሴቶችና ሕፃናት መነገድን በተመለከተ ባከናወነው ክትትል ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ምክክር አካሂዷል። በምክክሩም ክትትል በተደረገባቸው አፋር (ሰመራና ሎጊያ ከተማ)፣ አዳማ ከተማ፣ ወላይታ ዞን፣ ባሕር ዳር እና አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በምክክር መድረኩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ምላሽ አሰጣጥ ከተጣለባቸው የሕግ ግዴታ እና ከሰብአዊ መብቶች አኳያ በኮሚሽኑ የተደረገው ክትትል ሪፖርት ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሀገር ውስጥ የሰዎች ንግድ ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ላይ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም ባለግዴታዎች ድርጊቱን አስቀድሞ ለመከላከል፣ ለተጎጂዎች ጥበቃና ጊዜያዊ ድጋፍ ለመስጠት፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ እና ድርጊቱን ለመቆጣጠር ያላቸውን ትብብር የተመለከቱ ግኝቶች ለውይይት ቀርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከመጡባቸው ተቋማት ግዴታ አኳያ በኮሚሽኑ ክትትል ግኝቶች ላይ ያሏቸውን ተጨማሪ ሐሳቦች አጋርተዋል። እንዲሁም በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ተግባር በቂ ትኩረት ያልተሰጠውና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚሻና ወጥ የሆነ ሀገራዊ የምላሽ ስትራቴጂ ሊወጣለት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን በውይይታቸው ገልጸዋል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በምክክር መድረኩ በሰጡት ሐሳብ በብዛት ትኩረት የሚደረግበት ድንበር ተሻጋሪ የሆነው የሰዎች መነገድ መሆኑን ጠቅሰው የሀገር ውስጥ የሰዎች መነገድ ጉዳይ ግን በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው አስታውሰዋል። አክለውም በሀገር ውስጥ በሰዎች የመነገድ ተግባር በተለይም የሴቶችና ሕፃናት መነገድ ሰፊና ውስብስብ ችግር በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ በመግለጽ የሚመለከታቸው አካላት ከተጣለባቸው ግዴታ አንፃር የሀገር ውስጥ በሴቶችና ሕፃናት መነገድን ለመግታት በትስስር መሥራት እንዳለባቸው እና በኮሚሽኑ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች እንዲተገበሩ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚገባቸው በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡