የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጉራጌ ዞን እና በቀቤና ልዩ ወረዳ መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስና ያስከተለውን ጉዳት ከአካባቢው ነዋሪዎች በቀረበለት አቤቱታ መነሻነት ከጥቅምት 20 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በቦታው በመገኘት ጭምር ምርመራ ያከናወነ ሲሆን፣ አሁንም በአካባቢው ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታም በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡

ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች እና ምስክሮች ጋር 22 ቃለ-መጠይቆች አድርጓል፤ ከጉራጌ ዞን፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና ከቀቤና ልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች፣ በዞን እና በልዩ ወረዳ ደረጃ ከሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኘውን የኮማንድ ፖስት ኃላፊዎችን አነጋግሯል፣ በተጨማሪም ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 2 የቡድን ውይይቶች ተካሂደዋል። እንዲሁም ዘረፋ እና ውድመት ደርሶባቸዋል የተባሉ የግል እና የመንግሥት ተቋማትን ኮሚሽኑ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፤ ተጎጂዎች ሕክምና ካገኙባቸው የሕክምና ተቋማት የሕክምና ማስረጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አሰባስቧል።

በጉራጌ እና በቀቤና ማኅበረሰብ መካከል ከዚህ በፊትም የተለያየ መጠን ያለው ግጭት እና የሰላም ስምምነት ጥረት የነበረ ሲሆን፤ በተለይ ከቀቤና የልዩ ወረዳነት ምሥረታ ጋር በተያያዘ እና የልዩ ወረዳው መቀመጫን በተመለከተ በሁለቱ ማኅበረሰቦች አስተዳደሮች መካከል አለመግባባቱ እየተካረረና የግጭት አደጋው እየጨመረ መጥቶ እንደነበር መረዳት ተችሏል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች አሁንም ዘላቂ መፍትሔ ያልተሰጣቸው የመዋቅር እና የአስተዳደር ጥያቄዎች ለሰላም እና ደኅንነት እጦት እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ሆነው መቀጠላቸው እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ፤ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች ቅሬታና ጥያቄ የቀረበባቸውን አካባቢዎች ሁሉ ተዓማኒ በሆነና ተቀባይነት ባለው ሂደት በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመቻቹ ይገባል” ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “በወልቂጤ ከተማ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከሰተው ሁከት እና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት በመቀናጀትና ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ተጎጂዎች ሊካሱ ይገባል” ብለዋል፡፡

ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ስለተከሰተው የጸጥታ መደፍረስና ያስከተለው ጉዳት ዝርዝር ከዚህ በታች ተያይዟል፡፡


የምርመራው ዓላማ

  • በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መለየት እና ጥሰቶቹን የሚያሳዩ ትክክለኛ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እና መሰነድ፤
  • የአጥፊዎች ተጠያቂነት እንዲኖር የሚደረጉ ጥረቶችን ማገዝ፤ ለተጎጂዎች የተሟላ የካሳ፣ መልሶ ማቋቋም እና ድጋፍ እንዲደረግ ግፊት እና ውትወታ ማድረግ፤
  • በምርመራው ግኝቶች መሠረት ምክረ ሐሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ እርምጃዎች እንዲወሰዱና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እንዲሻሻል ማስቻል፤ ወደፊትም ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይከሰቱ መከላከል ናቸው፡፡

ምርመራው የተካሄደበትነ ዘዴ እና ወሰን

ኢሰመኮ የምርመራው ሥራ ተዓማኒነት፣ ተገቢነት እና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ እንዲረዳ የሚከተሉት የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎች ሥራ ላይ አውሏል፡፡  

  • ምርመራ በተካሄደባቸው ቦታዎች በየደረጃው ካሉ የመንግሥት መዋቅር አካላት፣ ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከተጎጂዎችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅና ውይይት፤
  • ግጭቱ በተከሰተባቸው ቦታዎች በአካል በመገኘት ስለጉዳዩ አጠቃላይ ሁኔታ ከሚመለከታቸውና ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በተናጠልና የቡድን ውይይት በማድረግ፣ በምልከታ የተገኘ መረጃ፣ የሕክምና ተቋማት ማስረጃዎች፣ የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃዎች እና ልዩ ልዩ የሰነድ ማስረጃዎች በማሰባሰብ የተከናወነ ነው፡፡
  • ይህ የምርመራ ሪፖርት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን እና በቀቤና ልዩ ወረዳ በተከሰተው ግጭት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው።

የማስረጃ ምዘና ደረጃ

ኢሰመኮ ይህንን ምርመራ ሲያከናውን የተጠቀመው የማስረጃ ምዘና ደረጃ በተመሳሳይ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ምርመራዎች እንዲሁም በዓለም አቀፍ አጣሪ ኮሚሽኖች ወይም የእውነት አፈላላጊ አካላት ጥቅም ላይ የሚውለውን “የምክንያታዊ አሳማኝነት” (reasonable grounds to believe) ተብሎ የሚታወቀውን የማስረጃ ምዘና መስፈርትን ነው። በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ የአንድ ጥሰት መፈጸም ወይም አለመፈጸምን አስመልክቶ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጉዳዩን አስመልክቶ ከተለያዩ ተዓማኒነት ካላቸው ምንጮች የተሰበሰቡ መረጃዎች እርስ በእርስ ተመሳሳይነት ያለው ወይም የማይጣረስ መረጃ መስጠታቸውን እና አንድ ምክንያታዊ የሆነን ሰው ሊያሳምን በሚችል አግባብ ስለ አንድ ነጠላ ክስተት ወይም ስልት እና አሠራርን የሚያሳይ ተደጋጋሚ ጥሰትን (አዝማምያ/pattern) የሚያስረዳ ሲሆን ነው።

ዳራ

የጉራጌ እና ቀቤና ብሔረሰብ በቀድሞ የደቡብ ክልል በአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡

በአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አደረጃጀት መሰረት የጉራጌ ዞን በ10 ወረዳዎች እና 5 ከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ቀቤና 23 ቀበሌዎችን ይዞ በልዩ ወረዳ ደረጃ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ እንዲቋቋም ለአዲሱ ክልል ምክር ቤት በቀረበው የውሳኔ ሐሳብና የምክር ቤቱ ውሳኔ ላይ የወልቂጤ ከተማን በሚመለከት የጉራጌ ዞን መቀመጫ እንደሆነና የቀቤና ልዩ ወረዳ መቀመጫን በሚመለከት ለወረዳው ነዋሪዎች አማካይ በሆነ ቦታ ላይ እንደሚመሠረት ይገልጻል፡፡ ሆኖም ግን የልዩ ወረዳው የምሥረታ ቦታ እና መቀመጫው የት ይሆናል የሚለው ጥያቄ አለመግባባት መፍጠር ጀምሮ ነበር፡፡ የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ኃላፊዎች ልዩ ወረዳው ወልቂጤን ማዕከል አድርጎ እንዲመሰረት እንደሚሹ ሲያሳውቁ፤ በአንጻሩ የጉራጌ ዞን እና የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ሕጋዊነት የለውም በማለት ተቃውመውታል፡፡

የቅርብ ጊዜው ግጭት አነሳስና ያስከተለው ጉዳት

መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም የቀቤና ልዩ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የቀቤና ልዩ ወረዳነት የምሥረታ በዓል መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ እንደሚካሄድ በይፋ መግለጫ አሳወቀ። መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የቀቤና ልዩ ወረዳን መግለጫ በመቃወም የቀቤና ልዩ ወረዳ ምሥረታ የጉራጌ ልዩ ዞን መቀመጫ ወልቂጤ ከተማ ላይ ሊካሄድ እንደማይገባ፣ ጉዳዩም ከከተማው መስተዳድር እውቅና ውጭ የተደረገ ሕገ ወጥ ሂደትና ጥሪ መሆኑንና በከተማው ግጭት የሚጋብዝ ስለሆነ አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ተግባር እንደሚያከናውን አስጠነቀቀ፡፡

ይህንኑ ተከትሎ በጉራጌ እና በቀቤና ማኅበረሰቦች መካከልም አለመግባባትና የወልቂጤ ከተማ የይገባኛል ጥያቄን በማባባስ የፖለቲካ ውጥረቱን እየጨመረው መጣ፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳደር ውጥረቱን ለማብረድ የልዩ ወረዳው ምሥረታ በወልቂጤ ከተማ እንዲከናወን፣ ነገር ግን በዓሉ የአደባባይ በዓል ከመሆን ይልቅ በቀቤና የባህል ማዕከል አዳራሽ እንዲከበር የሚል ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ሆኖም የቀቤና ልዩ ወረዳ ኃላፊዎች የጉራጌ ዞን ኃላፊዎች የምሥረታ በዓሉን ለማደናቀፍ ሞክረዋል፣ መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ለምሥረታ በዓሉ በክብር እንግድነት የመጡ ሰዎች መኪናዎች ተሰብረዋል፤ ማረፊያ ቦታ እንዳያገኙ ሆቴሎች ዝግ እንዲሆኑ ተደርጓል፣ የቀቤና ባህላዊ ልብስ የለበሱ ሰዎችን ማንገላታት እና የባህል ልብሳቸውን አስወልቆ በእሳት እስከ ማቃጠልና የበዓሉ ታዳሚ የነበሩ ሰዎችን መደብደብ ጭምር ተፈጽሞብናል በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

በአንጻሩ የጉራጌ እና የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች የልዩ ወረዳው የምሥረታ በዓል በሰላም እንዲከናወን ድጋፍ መሰጠቱን እና አመራሮቹም በምሥረታው ዝግጅት ላይ መሳተፋቸውን፤ ሆኖም የቀቤና ልዩ ወረዳ ኃላፊዎች በተቀራኒው “ወልቂጤ ከተማ የእኛ ናት፣ ከተሳካልን በሰላም ካልሆነ ግን በደም የእኛ እናደርጋታለን” የሚል ግጭት ቀስቃሽ ንግግር ሲያደርጉ ነበር በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

በእነዚህ ውጥረቶች መካከል ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠዋት ላይ ሁለት የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጆች ወልቂጤ ከተማ በሚገኘው የጉራጌ ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ አካባቢ በሚገኙ የተወሰኑ ወጣቶች ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ የዚህ ክስተት ወሬ መሰማቱን ተከትሎ በዚያው ዕለት ረፋዱ ላይ በወልቂጤ ከተማ በሚገኘው በድረዲን መስጊድ አካባቢ የቀቤና ብሔረሰብ ተወላጆች በተወሰኑ ወጣቶች ድብደባ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በአካባቢው መጠነ ሰፊ የሆነ ግጭት እና ረብሻ ተነስቷል፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የዐይን ምስክሮች እንደገለጹት በሁለቱም የአስተዳደር መዋቅር የሚገኙ የጸጥታ አካላት በግጭቱ ላይ ተሳትፎ ስለነበራቸው “አካባቢው ውጊያ የተካሄደበት ስፍራ ይመስል ነበር” በማለት የግጭቱን ከፍተኛነት መጠን ያስረዳሉ።

በዚህም ሁከት እና ረብሻ አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባልን ጨምሮ አራት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፣ ቢያንስ 114 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ የመንግሥት ቢሮዎች፣ የግለሰቦች መኖሪያና ንግድ ቤቶችና ንብረቶች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል፣ እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ ምርመራ በተደረገበት ወቅት በርካታ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቆላ ካባዳ፣ ዘቢሞላ፣ ፍቃዶ፣ ረካቦቃ፣ ገራባ እና ወሊሶ ከተማ ተጠልለው ይገኙ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች ምንም ዐይነት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸው ለልመና እንደተገደዱ ያስረዳሉ፤ እንዲሁም የሚቆዩበት ቦታ የሌላቸው ተፈናቃይ ሰዎች መኖራቸውን ጭምር መመልከት ተችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የዜጎች በሕይወት የመኖር፣ በመረጡት አካባቢ የመንቀሳቀስና የመኖር፣ ከመንግሥት የሕግ ጥበቃና ደህንነት የማግኘት፣ ንብረት የማፍራትና ከሕግ ውጪ ንብረታቸውን ያለማጣት መብት ተጥሷል፡፡

በመኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ በደረሰበት ድብደባ ሕይወቱ ስላለፈ ሰው የሟች ባለቤት በእለቱ የነበረውን ሁኔታ ስታስረዳ ” እሁድ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ቤት ውስጥ ቡና እያፈላሁ ሳለ በርካታ ወጣቶች በጎረቤት አጥር ሰብረው ሲገቡ፣ በሁኔታው የተደናገጠው ባለቤቴ ከተቀመጠበት ወደ ውጪ ሲወጣ ወጣቶቹ ይዘውት በነበረው ፌሮ (ብረት)፣ ቢላና በገጀራ ደጋግመው ከመቱት በኋላ እየጎተቱ ወደ ውጭ አወጡት፤ እኛ ለሕይወታችን ፈርተን ከቤት አልወጣንም ነበር። ጥለውት ሲሄዱ ነፍሱ ነበረች ነገር ግን ማንም ሊደርስልኝ ባለመቻሉ ወደ ሕክምና ተቋም ልወስደው አልቻልኩም” ብላለች፡፡ ባለቤቷ ሕይወቱ ካለፈ በኋላም ሬሳውን በወቅቱ ማንሳት እንዳልተቻለና የፌዴራል ፖሊሶች መጥተው አካባቢው ከተረጋጋ በኋላ የባለቤቷን ሬሳ ለማንሳት እንደቻሉ፣ እንዲሁም ባለቤቷ እርሷን ጨምሮ የ7 ሰዎች አስተዳዳሪ እንደነበር ለኮሚሽኑ አስረድታለች።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ስለተመለከተው ሁኔታ ሲያስረዳ “በግምት ከቀኑ 9፡30 ሰዓት አካባቢ ለሰፈር ልጆች ተደውሎ ዋቤ ወንዝ አካባቢ ከብቶች እንደተዘረፈ እና የድንጋይ መፍጫ ማሽን (ክሬሸር) እየተቃጠለ ነው” በማለት እንደተነገረው እና “ከሌሎች የሰፈሩ ወጣቶች ጋር ተሰብስበን ወደ ስፍራው እንደደረስን የደቡብ ክልል ፖሊስ መኪና በድንገት በመምጣት ተሰብስበው የቆሙ ሰዎች ላይ መተኮስ ጀመሩ፣ በዚህ በመደናገጥ ከአካባቢው ተበታተንን፣ የፖሊስ አባላቶቹ በተኮሱት ጥይት ተመቶ የወደቀ አንድ ሰው የፌዴራል ፖሊስ መኪና አንስቶት በአካባቢው ወደሚገኘው አልቢር ሃሰን ኤንጃሞ ጤና ጣቢያ ወሰዱት፤ ሆኖም ግን ጉዳቱ ከጤና ጣቢያው አቅም በላይ በመሆኑ ወደ ወሊሶ ሆስፒታል የተወሰደ ቢሆንም ሕይወቱን ማትረፍ ሳይቻል እንደቀረ ለኮሚሽኑ አስረድቷል።

ሌላ በዚሁ ቦታ የነበረ የአካባቢው ነዋሪ ስለሁኔታው እንዲህ በማለት አስረድቷል፡፡ “በቦታው እንደደረስን በእሳት እየተቃጠለ የነበረው ማሽን ጠፍቶ ነበር፤ ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ወጣቶች ተሰብስበን በቆምንበት የታጠቁ የደቡብ ክልል ፖሊስ አባላት በተሽከርካሪ ላይ ሆነው እየተኮሱ በቦታው ደረሱ፤ ወዲያው በድንጋጤ ከአካባቢው ተበተንን” በማለት፣ በተተኮሰው ጥይት ግራ እጁ ላይ ጉዳት እንደደረሰትና እርሱን ጨምሮ አብረው የነበሩ 3 ሰዎች በጥይት ጉዳት እንደደረሰባቸው ለኮሚሽኑ አስረድቷል።

ነዋሪነቱ ወልቂጤ ከተማ የሆነ እና በንግድ ሥራ የሚተዳደር አንድ የአካል ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ ደግሞ፣ የተሰባሰቡ ወጣቶች ወደሚሠራበት ምግብ ቤት እንደመጡና “የጉራጌ ዞን አመራሮችን የምትመግበው አንተ ነህ?” በማለት በያዙት ድንጋይ ጭንቅላቱንና እና ጀርባውን ደጋግመው እንደመቱት በመቀጠልም ምግብ ቤቱን በመሰባበር ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱበት አስረድቷል፡፡

ሌላ ተጎጂ ወልቂጤ ከተማ በሚገኘው የንግድ ቦታው ብዛት ያላቸው ወጣቶች እንደመጡ እና ሱቁን እንዲዘጋ በማዘዝ ጭንቅላቱን በድንጋይ በመምታት ጉዳት እንዳደረሱበት አስረድቷል።

ኮሚሽኑ ያነጋገረው አካል ጉዳት የደረሰበት አንድ የባጃጅ ሹፌርም የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ባለበት ወቅት የተሰባሰቡ ወጣቶች ጥቃት ሊያደርሱበት ሲጠጉት፣ ለማምለጥ ሲሞክር በጥይት ተመቶ የአካል ጉዳት እንደደረሰበት አስረድቷል።

ኮሚሽኑ በግጭቱ ምክንያት መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ቦታቸው የተዘረፉባቸውን ስፍራዎች ተዘዋውሮ ጎብኝቷል። በርካታ ቁጥር ያላቸው የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ቦታዎች ተሰባብረዋል፤ በውስጣቸው የሚገኙ ንብረቶችም ተዘርፈዋል፡፡ በቀቤና ልዩ ወረዳ 3 የመንግሥት ተቋማት የሆኑት የልዩ ወረዳው መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ ግብርና ቢሮ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮዎች ተሰባብረዋል፤ በውስጡ የሚገኙ ንብረቶችም ተዘርፈዋል፡፡ በጉራጌ ዞን በተመሳሳይ የዞኑ ግብርና ቢሮ መስታወቶች ተሰባብረዋል፤ በውስጡ የሚገኙ ንብረቶችም ተዘርፈዋል፡፡

ነዋሪነቱ በወልቂጤ ከተማ የሆነ አካል ጉዳተኛ ግለሰብ ለኮሚሽኑ እንደገለጸው የተሰባሰቡ ወጣቶች የመኖሪያ ቤቱን በር ገንጥለው ሲገቡ፣ ሕይወቱን ለማትረፍ የጎረቤት ቆርቆሮ አጥርን ገንጥሎ እንደወጣና ጎረቤቶቹ እንደደበቁት፣ የልዩ ኃይል አዛዥ የሆነ አንድ ግለሰብ ጋር ስልክ ደውሎ ኃይል ይዞ ስለመጣ ሕይወቱ ሊተርፍ እንደቻለ፣ ሆኖም ግን ወጣቶቹ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ንብረቶችን እንደዘረፉበት ያስረዳል፡፡

ሌላ ተጎጂ ወጣቶች ወደ ቤቱ በመምጣት በመኖሪያ ቤት ውስጥ የነበረች እህቱን በመምታትና በተሽከርካሪ በመጠቀም የቤቱን ሙሉ እቃ፣ የቤቱን 11 በሮች በመፍታት እንዲሁም ሮቶ በመባል የሚታወቀውን የውሃ ማጠራቀሚያ ጭምር መውሰዳቸውንና መውሰድ ያልቻሉትን እቃዎች በመሰባበር ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱበት አስረድቷል፡፡

የጉራጌ ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ የሚኖሩ የቀቤና ብሔረሰብ ተወላጆች፣ እንዲሁም የቀቤና ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች መኖሪያ ቤቶቻቸው ተለይተው ጥቃት እንደደረሰባቸውና የቤት እና የንግድ ዕቃዎቻቸው እንደተዘረፈባቸው ገልጸው ጥቃት ፈጻሚዎቹ የተሰባሰቡ ወጣቶች ስለታማ ነገሮችን፣ ዱላ እና ድንጋይ በመያዝ ዘረፋ እንደፈጸሙ ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው ተጎጂዎች መካከል አካላዊ ድብደባ የደረሰባቸው ሴቶች እና አዛውንቶች ይገኙበታል፡፡ አንድ የአዕምሮ ሕመም ያለበት ወጣት ማታ ላይ በከተማው ሲንቀሳቀስ ፖሊሶች ይዘውት ባልታወቀ ቦታ በማሰር ጉዳት እንዳደረሱበት ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ምስክሮች ገልጸዋል።

ከቀቤና ልዩ ወረዳም ሆነ ከጉራጌ ዞን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች በእለቱ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዳልሰጡ፣ ይልቁን አባባሽ ድርጊቶች ላይ ሲሳተፉ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፣ በሁለቱም ወገኖች ያሉ የሚመለከታቸው የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት በበኩላቸው ለክስተቱ አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጡ የነበሩ እንጂ ማንኛውም ዐይነት አባባሽ ድርጊት ላይ እንዳልተሳተፉ ይናገራሉ።

ይህ ምርመራ በተከናወነበት ወቅት በሁከቱ ተሳታፊ ከነበሩ ከሁለቱም ወገኖች ግጭቱን በማነሳሳት እና በድርጊቱም ተሳታፊ ናቸው በሚል የሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ የተጀመረ ምርመራና የተወሰደ እርምጃ ገና አልነበረም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሁለቱም ወገኖች በግጭቱ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ አካል ጉዳት ለደረሰባቸው፣ መኖሪያ ቤታቸው እና የንግድ ቦታቸው ለወደመባቸው ተጎጂዎች ካሳ አልተከፈለም፡፡ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለሚገኙ ሰዎችም የተደረገላቸው ድጋፍ አልነበረም፡፡