የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን 2ኛው የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የተመለከተ ባለ 35 ገጽ የዘርፍ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ የተስተዋሉ መልካም እመርታዎች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎች እና ምክረ ሐሳቦችን በዝርዝር አካቷል።
ኢሰመኮ ሪፖርቱን ያዘጋጀው በበጀት ዓመቱ ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራዎች፣ በግለሰቦች እና በሲቪክ ማኅበራት የቀረቡ አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶች እና ልዩ ልዩ የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ግብአቶችን መሠረት በማድረግ ነው። በተጨማሪም ከመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እና ከአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ማኅበራት አባላት ጋር ከተደረጉ ቃለመጠይቆች እና ከሌሎች ሰነዶች የተገኙ መረጃዎች በሪፖርቱ ተካተዋል።
ይህ የዘርፍ ሪፖርት የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን በሕይወት የመኖር መብት፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት ሁኔታ፣ አስቻይ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ መረጃ የማግኘት፣ ትርጉም ያለው ተሳትፎ የማድረግ፣ የመሥራት መብቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ማኅበራት የእንክብካቤ ማእከላት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጓል። በተጨማሪም የአካል ድጋፍና ተሐድሶ አገልግሎት የማግኘት መብት፣ የአረጋውያን የአካል ደኅንነት መብት፣ ለተደራራቢ የመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁኔታ እንደ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት፣ ሴት አካል ጉዳተኞች እንዲሁም አረጋውያን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ አካል ጉዳተኞች ሁኔታ ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።
በሪፖርቱ ከተካተቱ መልካም እመርታዎች መካከል ጤና ሚኒስቴር ባሻሻለው የጤና ፖሊሲ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መካተቱ፣ ረቂቁ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ በልዩ ሁኔታ የጡረታ ጊዜን ማራዘም የሚቻልበትን ሁኔታ አካቶ መዘጋጀቱ፣ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት መገንባቱ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዐይነ ስውራን ተደራሽ ያልነበረውን የሞባይል መተግበሪያውን ተደራሽ በሆነ መንገድ ማበልጸጉ ይገኙበታል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማት መንገዶች ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረቶች መደረጋቸው እና የመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ እየተሠራ መሆኑ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት/CRPD/ አፈጻጸምን የሚከታተል ክልላዊ ኮሚቴ መቋቋሙ በበጀት ዓመቱ ከተለዩ እመርታዎች መካከል ናቸው።
በሌላ በኩል ሪፖርቱ በበጀት ዓመቱ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ዙሪያ የተስተዋሉ አሳሳቢ ጉዳዮችንም አካቷል፡፡ በትጥቅ ግጭቶች ዐውድ ውስጥ በሚፈጠሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሳቢያ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለንብረት ውድመት/ዘረፋ መዳረጋቸው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ እንዲሁም በሰብአዊ ድጋፍ እጥረት ሳቢያ አረጋውያን ለምግብ እጥረት/ለረሃብ መጋለጣቸው፤ የአረጋውያን እና አእምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ ማእከላት ውስጥ የሚስተዋል እና በተለይም ሴት የአእምሮ ሕሙማን ላይ ያተኮረ ጾታዊ ጥቃት መኖሩ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታና በትጥቅ ግጭቱ ሳቢያ በሚጣሉ የሰዓት እላፊና የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት በአነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ሥራ ዘርፍ የሚተዳደሩ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ለችግር መጋለጣቸው ተጠቃሽ ናቸው።
እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ምክንያት አመቺ እና ተደራሽ ምትክ ቦታዎች ባልተሰጠበት ሁኔታ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን እንዲነሱ መደረጉ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውሶች መጋለጣቸው፤ እንዲሁም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ብዛት ከ10 በመቶ የማይበልጥ መሆኑ አሳሳቢ በሚል የተለዩ ሁኔታዎች ናቸው።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ የተለዩትን አሳሳቢ ሁኔታዎች ለመቅረፍ ብሎም የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ሰብአዊ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማክበር፣ ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት ያስችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችም አመላክቷል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ተገቢውን ከለላና ሰብአዊ እርዳታ የማያገኙ መሆኑን ጠቅሰው ሰላምን ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። አክለውም የአካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን መብቶች ማስጠበቅ እና ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ፤ እንዲሁም ለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሔን የመስጠት ዋና ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ ይህንኑ በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበው፤ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ ድርጅቶች እና የልማት አጋሮች መንግሥትን በዚህ ረገድ እንዲያግዙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።