መግቢያ

ውሃ ለሕይወት እና ጤና መሠረታዊ የሆነ ውስን የተፈጥሮ ሀብት ከመሆኑም በተጨማሪ የሰው ልጅ ሰብአዊ ክብሩ ተጠብቆ እንዲኖር እንዲሁም ሌሎች ሰብአዊ መብቶቹን እንዲጠቀም ለማስቻል መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ሲሆን በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችም ጥበቃ የሚደረግለት መብት ነው። የውሃ ሀብት ጥበቃና ልማት ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና ተጨባጭ ተግባራትን ለማበረታታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ በየዓመቱ መጋቢት 13 የዓለም የውሃ ቀን ሆኖ ይከበራል። ይህም ማብራሪያ ቀኑን በማስመልከት የውሃ መብት ምንነት፣ ጥበቃ፣ ይዘት እና የመንግሥታት ግዴታዎችን አስመልክቶ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተዘጋጀ ነው።

የውሃ መብት ምንድን ነው?

የውሃ መብት ሁሉም ሰው ለግሉ እና ለቤት ውስጥ አገልግሎት በቂ የሆነ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ተቀባይነት ያለው፣ በአካል ተደራሽ እና በዋጋ ተመጣጣኝ/affordable የሆነ ውሃ የማግኘት መብት ሲሆን በውስጡ ሌሎች ነጻነቶችን/freedoms እና መብቶችን/entitlments እንደሚይዝ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ የውሃ መብትን አስመልክቶ የሰጠው አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 15 ያስረዳል። ለአብነትም የውሃ መብት በአንድ በኩል ነባራዊውን የውሃ አቅርቦት በቀጣይነት የመጠቀም እንዲሁም በዘፈቀደ ከሚደረግ የአገልግሎት መቋረጥ ወይም የውሃ አቅርቦት መበከል እና መሰል ጣልቃ ገብነቶች ነጻ የመሆን፤ በሌላ በኩል የውሃ መብትን በእኩልነት የመጠቀም ዕድልን የሚያረጋግጥ የውሃ አቅርቦት እና አስተዳደር ሥርዓት የማግኘት መብትን በውስጡ ያካትታል።

የውሃ መብት በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች የተሰጠው ጥበቃ ምን ይመስላል?

በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 11/ 1 ማንኛውም ሰው በቂ ምግብ፣ ልብስና መኖሪያ ቤትን ‘ጨምሮ’ ለራሱ እና ለቤተሰቡ በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት እና የኑሮ ሁኔታውን በቀጣይነት የማሻሻል መብት እንዳለው ይደነግጋል። በዚህ ድንጋጌ ውስጥ ያለው ‘ጨምሮ’’ የሚለው አገላለጽ ዝርዝሩ ገዳቢ/exhaustive እንዳልሆነና በግልጽ ከተዘረዘሩት የምግብ፣ ልብስና መኖሪያ ቤት መብቶች በተጨማሪ ከመብቱ የሚመነጩ እንዲሁም መብቱን እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች መብቶችን በውስጡ የሚያካትት መሆኑን መረዳት ይቻላል። ውሃ የሰው ልጅ በሕይወት እንዲኖር ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ አቅርቦቶች መካከል አንዱ እና ዋናው ሲሆን ከበቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት የሚመነጭ ሰብአዊ መብት መሆኑን የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ይገልጻል። እንዲሁም የውሃ መብት በድንጋጌው ስር በግልጽ ከተካተቱት የመኖሪያ ቤት እና የምግብ መብት፣ በቃልኪዳኑ አንቀጽ 12 ስር ከተመላከተው ሊደረስበት የሚችለውን ከፍተኛውን የአካል እና የአእምሮ ጤና ደረጃ የማግኘት መብት እንዲሁም በሕይወት የመኖር መብት እና ከሰብአዊ ክብር መብት ጋር ሊነጣጠል በማይቻል መልኩ የተቆራኘ መብት መሆኑን አጠቃላይ ትንታኔው ያስረዳል።

ከዓለም አቀፉ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ቃል ኪዳን በተጨማሪ የውሃ መብት በሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ መግለጫዎች እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) ሰነዶች ስር እውቅና ተሰጥቶታል። እ.ኤ.አ. በ2030 ደኅንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ እና የንጽሕና አጠባበቅ አቅርቦትን ማረጋገጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች ግብ 6 ተካቶ ይገኛል።

በአህጉር ደረጃም የውሃ መብት በአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር ውስጥ እውቅና ካገኙ በክብር የመኖር መብት (አንቀጽ 4)፣ የጤና መብት (አንቀጽ 16) እና በጤናማ አካባቢ የመኖር መብት (አንቀጽ 24) ጣምራ ንባብ መሠረት ጥበቃ የተደረገለት መሆኑን የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ ውሳኔዎቹ ገልጿል። በተጨማሪም የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2019 በአፍሪካ የውሃ መብትን የተመለከተ መመሪያ ያወጣ ሲሆን፤ ሀገራት መብትን መሠረት ያደረገ የውሃ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም በቂ ውሃ የሌላቸውን ወይም ያለማግኘት ስጋት ውስጥ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መለየት እና የመብቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ የአፍሪካ የሕጻናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር እንዲሁም የአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) ድንጋጌዎች ውስጥ የውሃ መብት በግልጽ እውቅና ተሰጥቶታል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የውሃ መብት ያለውን የሕግ ጥበቃ ስንመለከት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ቃልኪዳን በ1993 ዓ.ም. ያጸደቀች በመሆኗ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት ስምምነቱ የሀገሪቱ የሕግ አካል በመሆን የውሃ መብትን የማረጋገጥ ግዴታ በመንግሥት ላይ ይጥላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 41(3) ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ‘ማኅበራዊ አገልግሎቶች ’ በእኩልነት የመጠቀም መብትን ሲደነግግ፤ አንቀጽ 41(4) መንግሥት ‘ማኅበራዊ አገልግሎቶችን’ ለሕዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሃብት የመመደብ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። በእነዚህ ድንጋጌዎች ሥር ‘ማኅበራዊ አገልግሎቶች‘ የሚለው አገላለጽ የውሃ አገልግሎትን የሚያካትት ተደርጎ ሊተረጎም የሚችል ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የውሃ መብት በግልጽ የተጠቀሰው ብሔራዊ የፖሊሲ መርሖች እና ዓላማዎችን በሚዘረዝረው ምዕራፍ ውስጥ በአንቀጽ 90(1) ላይ ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሪቱ ዐቅም በፈቀደ መጠን የንጹሕ ውሃ አቅርቦት እንዲኖረው እንደሚደረግ ይደነግጋል። 

የውሃ መብት ይዘቶች ምን ምን ናቸው?

እንደ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ የውሃ መብትን በመሠረታዊነት ለማረጋገጥ የሚከተሉት ሦስት ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል። እነዚህም፦

(ሀ) ተገኝነት፦ ሁሉም ሰው ለግል እና ለቤት ውስጥ አገልግሎቶች በቂ የሆነ የውሃ አቅርቦት በቀጣይነት ማግኘት ይኖርበታል። ውሃ በዋናነት ለመጠጥ፣ ለእጥበት፣ ምግብ ዝግጅት፣ የግል እና የቤት ንጽሕና መጠበቅ እና መሰል አገልግሎቶች የሚውል ሲሆን በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መመሪያ መሠረት የውሃ አቅርቦት በመሠረታዊነት ተገኚ ሆኗል የሚባለው አንድ ሰው በቀን ቢያንስ በትንሹ 20 ሊትር ውሃ ሲያገኝ ነው።

(ለ) ጥራት፦ ለግል እና ለቤት ውስጥ አገልግሎቶች የሚውል ውሃ ደኅንነቱ የተጠበቀ ማለትም ለጤና ጎጂ ከሆኑ ጥቃቅን ተሕዋስያን፣ ኬሚካላዊ ንጥረነገሮች እና ጨረራ ነጻ መሆንና ተቀባይነት ያለው ቀለም፣ ሽታ እና ጣዕም ሊኖረው እንደሚገባ የኮሚቴው ትንታኔ ያስረዳል።

(ሐ) ተደራሽነት፦ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኘው ውሃ እና የውሃ ተቋማት እና አገልግሎቶች ያለ አድልዎ ለሁሉም ሰው ተደራሽ መሆን አለባቸው። ተደራሽነት የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን የሚከተሉትን ሁኔታዎች በውስጡ ይይዛል፦

  1. አካላዊ ተደራሽነት፡ ውሃ እና በቂ የውሃ ተቋማት እና አገልግሎቶች ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ በሆነ ተገቢ አካላዊ ርቀት ውስጥ መገኘት ይኖርባቸዋል። እንደ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መመሪያ አካላዊ ተደራሽነት በመሠረታዊ ደረጃ ተሟልቷል ለማለት የውሃ አቅርቦቶች ከአንድ ኪሎሜትር ወይም ከሰላሳ ደቂቃ ጉዞ ባነሰ ርቀት ውስጥ መገኘት ይኖርባቸዋል።
  2. ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ፡- ውሃ እና የውሃ ተቋማት እና አገልግሎቶች በዋጋ ረገድ ለሁሉም ተመጣጣኝ/affordable በሆነ መልኩ ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል። ይህም ማለት ከውሃ ጋር የተያያዙ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ወጪዎች እና ክፍያዎች ከማኅበረሰቡ የመክፈል ዐቅም ጋር ተመጣጣኝ የሆኑና በሌሎች የቃል ኪዳኑ መብቶች የመጠቀም ዐቅምን የማይገድቡ መሆን ይኖርባቸዋል።
  3. ከአድልዎ ነጻ መሆን ፡- ውሃ ፣ የውሃ ተቋማት እና አገልግሎቶች በሕግም ሆነ በአሠራር ማናቸውም አድሎ ሳይደረግ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ለሁሉም ተደራሽ መሆን ይኖርባቸዋል።
  4. የመረጃ ተደራሽነት ፡- ከውሃ ፣ከውሃ ተቋማት እና አገልግሎቶች ጋር የተያያዙ መረጃዎች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ መሆንና እነዚህን መረጃዎች የመፈለግ፣ የመቀበል እና የማስተላለፍ ነጻነት በተገቢው መልኩ መከበሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የውሃ መብትን አስመልክቶ መንግሥታት ያሉባቸው ግዴታዎች ምንድን ናቸው?

ሀገራት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችን ካጸደቁ በኋላ በሰነዶቹ ውስጥ የተመላከቱትን መብቶች በግዛታቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም መሠረት በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 2(1) ላይ እንደተቀመጠው ቃልኪዳኑን ያጸደቁ ሀገራት የውሃ መብትን ሙሉ በሙሉ እውን ለማድረግ ተጨባጭ፣ የታቀዱ እና የታለሙ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የሚያስገድድ እንደሆነ እ.ኤ.አ. በ1990 የወጣው የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 3 ያመላክታል። የውሃ መብት ልክ እንደ ሁሉም ሰብአዊ መብቶች በሀገራት ላይ ሦስት ዓይነት ግዴታዎችን ይጥላል። እነዚህም የማክበር፣የመጠበቅ እና የማሟላት ግዴታዎች ሲሆኑ ከእነዚህ ግዴታዎች ውስጥ አንዱን አለመፈፀም የውሃ መብት ጥሰት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የማክበር ግዴታ 

የማክበር ግዴታ መንግሥት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመብት ባለቤቶች መብታቸውን ሲጠቀሙ ያለአግባብ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብን ይጠይቃል። ስለዚህም ከውሃ መብት ጋር ተያይዞ መንግሥት በቂ ውሃ ማግኘትን የሚከለክል ወይም የሚገድብ ማንኛውንም ተግባር ከመፈጸም፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የውሃ አቅርቦትን ከመቀነስ ወይም ከመበከል እንዲሁም በግጭት ወቅት የውሃ አገልግሎቶችን እና መሠረተ ልማቶችን ከመገደብ እና ከማጥፋት መቆጠብ እንዳለበት የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ያብራራል።

የመጠበቅ ግዴታ 

የመጠበቅ ግዴታ መንግሥት የመብት ባለቤቶች መብታቸውን ሲጠቀሙ ሦስተኛ ወገኖች ጣልቃ እንዳይገቡ የሚከለክሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ ይጠይቃል። ይህ ግዴታ የሚጣሰው መንግሥት የመብት ባለቤቶች በሦስተኛ ወገኖች ከሚደርስባቸው የመብቶች ጥሰት ለመጠበቅ ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎችን ካልወሰደ ወይም መብቶቹ ተጥሰው ሲገኙ እልባት ካልሰጠ ነው። በዚህም መሠረት መንግሥት ሕግ ማውጣትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ እና ውጤታማ እርምጃዎችን በመውሰድ ሦስተኛ ወገኖች የውሃ መበከልን እንዳያስከትሉ እና ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የተፈጥሮ የውሃ ሃብቶችን እንዳይጠቀሙ የመከልከል፤ ሦስተኛ ወገኖች በውሃ አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ከሆነ አቅርቦታቸው ተገኚ፣ ተደራሽ እና ጥራት ያለው መሆኑን የማረጋገጥ እንዲሁም ጥሰት ፈጽመው ሲገኙ ተገቢውን ቅጣት መወሰዱን ማረጋገጥ ይኖርበታል።

የማሟላት ግዴታ

የማሟላት ግዴታ መብትን ለመጠቀም የሚያስችሉትን ሁኔታዎች ማመቻቸት፣ የማቅረብ እና መብቱን የማሳደግ ወይም የማስተዋወቅ ግዴታዎችን ያጠቃልላል። በዚህም መሠረት ይህ ግዴታ መንግሥታት በሀገራዊ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ለውሃ መብት በቂ እውቅና መስጠትን ጨምሮ መብትን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ተገቢውን የሕግ፣ የአስተዳደር፣ የበጀት፣ የዳኝነት እና ሌሎች እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይጠይቃል።