የፕሬስ ነጻነት
የተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ. 1993 የፕሬስ ነጻነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ግንቦት 3 ቀን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀን[1] ይከበራል።
በዚህ ዓመት ትኩረቱን ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial intelligence) በፕሬስ ነጻነት እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ላይ በማድረግ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጎ ካልሆኑ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጽዕኖዎች ይልቅ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለፕሬስ ነጻነት እና ለዴሞክራሲ እድገት የሚያበረክተውን በጎ አስተዋፆ ማረጋገጥ ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ግንቦት 3 ቀን 2025) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ32ተኛ ጊዜ በብራስልስ ከተማ ተከብሯል።[2] ይህ ማብራሪያ ይህንኑ ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን የፕሬስ ነጻነትን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር ይረዳል።
የፕሬስ ነጻነት ምንድን ነው?
ፕሬስ ማለት ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅ ወይም ለማዝናናት በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በኢንተርኔት እና በተለያዩ ማሰራጫ ዘዴዎች በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በምስል፣ በቪድዮ፣ በግራፊክስ፣ በአኒሜሽን እና ሌሎች ቴክኖሎጂ ባፈራቸው ዐይነተ ብዙ አማራጮች አማካኝነት የሚቀርብ የሕትመት እና የቴሌቪዥን ስርጭት ተግባር ነው።[1] ፕሬስን በመጠቀም የተለያዩ ሐሳቦችን፣ አመለካከቶችን እና መረጃዎችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ማቅረብ፣ ማሳተም እና ማሰራጨት ደግሞ የፕሬስ ነጻነት በመባል ይታወቃል። የፕሬስ ነጻነት መከበር እና መጠበቅ ሌሎች መብቶችንም ለመተግበር እና ለመጠቀም አስተዋፆ ያደርጋል። ለምሳሌ ፕሬስን በመጠቀም ሰዎች ሐሳቦቻቸውን በነጻነት ይገልጻሉ፣ የመረጃ ተደራሽነት ይሰፋል፣ በመረጃ ልውውጦች ምክንያት የሰዎች ንቃተ ኅሊና ይጨምራል፣ ሰዎች የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነጻነቶቻቸውንም እንዲጠቀሙ ዕድል ይሰጣል፣ በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ያስችላል እንዲሁም ለማኅበረሰብ ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉልህ ሚና ይጫወታል።
የፕሬስ ነጻነት በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች የተሰጠው ጥበቃ ምን ይመስላል?
በተለያዩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ሕጎች መሠረት የፕሬስ ነጻነት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ውስጥ የሚካተት ነው። የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 19 ንኡስ አንቀጽ 2 መረጃንና ማንኛውንም ዐይነት ሐሳብ ያለምንም የድንበር ገደብ በቃል፣ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በስነ ጥበብ ወይም በሌላ የመገናኛ ዘዴ የመፈለግ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ውስጥ እንደሚጠቃለል ደንግጓል። የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 19፣ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 21 እና የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 13 የፕሬስ ነጻነትን በግልጽ የደነገጉ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎች ናቸው።
በአህጉር ደረጃ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 9 እንዳስቀመጠው ማንኛውም ሰው መረጃ የመቀበል፣ ሐሳቡን የመግለጽ እና የማሰራጨት መብት አለው። ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 7፣ በአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር አንቀጽ 4፣ በአፍሪካ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እና የመረጃ ተደራሽነት መርሖዎች መግለጫ ክፍል 2 እና በሌሎች የተለያዩ አህጉራዊ የመብት ሰነዶች ላይ ጥበቃ ተሰጥቶታል። የፕሬስ ነጻነት ሐሳብን የመግለጽ መብት ውስጥ የሚካተት በመሆኑ እነዚህ ሰነዶች ለፕሬስ ነጻነትም እውቅና የሚሰጡ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከላይ የተገለጹት ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች አባል ሀገር በመሆኗ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ 4 መሠረት እነዚህ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ስለ ፕሬስ ነጻነት በሰፊው ደንግጓል። በአንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 4 መሠረት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦች እና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነጻነት እና የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሕግ መሠረት የተቋቋመ እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ ተቋም ሲሆን በሀገሪቱ የፕሬስ አገልግሎት የሚስፋፋበትን እና በተስማሚ ቴክኖሎጂ የሚደራጅበትን ሁኔታ በማጥናት ሐሳብ የማቅረብ እና ፈቃድ ሲያገኝ ደግሞ ሥራ ላይ የማዋል ሥልጣን የተሰጠው ድርጅት ነው።[2]
የፕሬስ ነጻነት ምን ምን መብቶችን ያካትታል?
በአፍሪካ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እና የመረጃ ተደራሽነት መርሖች መግለጫ እና ዊንድሆክ መግለጫ በመባል የሚታወቀው በአፍሪካ የፕሬስ ነጻነትን እና ብዝኃነትን ለማስፋፋት የወጣው መግለጫ ፕሬስን ጨምሮ የመገናኛ ብዙኃን ነጻ እና ብዝሀነትን የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ እንደሚገባ ደንግገዋል። መግለጫዎቹ ባስቀመጧቸው መርሖዎች መሠረት መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አመለካከቶችን፣ ሐሳቦችን እና መረጃዎችን በማንሸራሸር ብዝሀነትን የሚያንጸባርቁ እና የሚያቀርቧቸው ይዘቶች ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ፣ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው አካላት እና ከሌሎች ጣልቃ ገብነት በጸዳ ሁኔታ ነጻነታቸው ተጠብቆ የሚሰሩ አካላት መሆን አለባቸው።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 3 ሥር እንደተጠቀሰው የፕሬስ ነጻነት የቅድሚያ ምርመራ (censorship) ክልከላን እንዲሁም የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብትን ያካትታል። ይዘቶቻቸውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሚያዘጋጁ እና ከቅድሚያ ምርመራ የጸዱ እንዲሁም ብዝሀነት ያላቸውን ሐሳቦች እና መረጃዎችን የሚያንሸራሽሩ ነጻ የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ተደራሽነትን ያሰፋሉ።
የፕሬስ ነጻነትን ጨምሮ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ከማረጋገጥ አንጻር መንግሥታት ያሉባቸው ግዴታዎች
በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 19 ላይ በተገለጸው መሠረት የቃልኪዳኑ አባል ሀገራት የፕሬስ ነጻነትን ጨምሮ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማረጋገጥ አለባቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ የቃል ኪዳኑ አባል ሀገራት ማንኛውንም ዐይነት ሐሳብ እና መረጃ የመፈለግ፣ የመቀበል እና የማካፈል መብት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በሕትመት፣ በስነ ጥበብ ወይም በሌላ በማንኛውም ዐይነት የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች በኩል እንዲረጋገጥ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ግዴታዎችን ያጠቃልላሉ።
- ሀገራት ላይ የተጣለው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የማክበር ግዴታ የሀገር ውስጥ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና የመንግሥት ድርጊቶች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንደማይጥሱ ማረጋገጥን እና በመገናኛ ብዙኃን መረጃ ይዘቶች ላይ ቅድመ ምርመራ አለማከናወንን ያካትታል።
- ሀገራት ላይ የተጣለው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የማስከበር ግዴታ የሰዎች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳይጣስ መከላከልን እና መብቶቹ ተጥሰው ሲገኙ ተገቢውን እርምጃ መውሰድን ያካትታል።
- ሀገራት ላይ የተጣለው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የማሟላት ግዴታ መንግሥት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማረጋገጥ የሚወስዳቸውን በጎ እርምጃዎች ማለትም የመረጃ ተደራሽነትና ብዝሀነትን ማስፋፋትን እና ሰዎች ሐሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ያካትታል።
በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን እና በሌሎች አህጉራዊ እና ሀገራዊ ሕጎች በተጠቀሰው መሠረት ሀገራት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ ለማድረግ፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ ለሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ልዩ ጥበቃ የሚያደርጉ ሕጎችን ማውጣት እና መተግበር፣ የጋዜጠኞችን እና የሌሎች የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾችን የዘፈቀደ እስር እና ጥቃት ማስቆም፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጥሱ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ፣ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምን እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በተመለከተ ለሕዝብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የፕሬስ ነጻነትን ጨምሮ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው በሕግ መሠረት እና የሌሎች ሰዎችን መብትና ክብር ለመጠበቅ፣ የሀገር ደህንነትን ወይም የሕዝብ ስርዓትን፣ የሕዝብ ጤናን ወይም ሞራልን ለመጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ መንግሥታት በማንኛውም ሁኔታ የፕሬስ ነጻነትን ጨምሮ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን መገደብ አይችሉም።
[1] የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ/ማሻሻያ/ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1308/2016፣ የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 1 እና 2
[2] የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1151/2011፣ የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 18
[1] በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ምክረ ሐሳብ መሠረት የተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ. 1993 ዓ.ም. የፕሬስ ነጻነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ1992 ዓ.ም. የዊንድሆክ መግለጫ በመባል የሚታወቀው በአፍሪካ የፕሬስ ነጻነትን እና ብዝኃነትን ለማስፋፋት የወጣው መግለጫ ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት ቀን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀን ሆኖ እ.ኤ.አ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ ግንቦት 3 ቀን ላይ በተለያዩ ርእሶች በመከበር ላይ ይገኛል። ዩኔስኮ በበኩሉ ግዊሌርሞ ካኖ ኢሳዛ የተባለ ጋዜጠኛ ሕትመቶች ላይ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ምክንያት እ.ኤ.አ በ1986 ዓ.ም. ኮሎምቢያ ውስጥ በመገደሉ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ቀን ሲከበር ጋዜጠኛውን ለማስታወስ ግዊሌርሞ ካኖ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት ለፕሬስ ነጻነት ለታገለ አንድ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ለሚገኝ ግለሰብ ወይም ተቋም በየዓመቱ ይሸልማል። የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በየዓመቱ የተለያዩ ሀገራት ላይ የሚከበር ሲሆን 26ተኛው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን የመገናኛ ብዙኃን ለምርጫ እና ለዴሞክራሲ ያላቸው ሚና ላይ በማተኮር በ2011 ዓ.ም. ( እ. ኤ. አ. በ2019) ኢትዮጵያ ወስጥ መከበሩ ይታወሳል።
[2] https://www.unesco.org/en/articles/world-press-freedom-day-2025-signature-event-reporting-brave-new-world-impact-artificial