የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሕክምና ባለሙያዎች በሕክምና ተቋማት ውስጥ በማድረግ ላይ የሚገኙት የሥራ ማቆም አድማ እንዲሁም ይህንን ተከትሎ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳያስከትሉ ትኩረት ሊሰጣቸው እና አፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚገባ ያሳስባል።
ኢሰመኮ አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች የደመወዝ እና ከሥራ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን መንግሥት እንዲመልስ ሰጥተናል ያሉት የ30 ቀናት የጊዜ ገደብ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. መጠናቀቁን ተከትሎ በመንግሥት እና በሕክምና ባለሙያዎች በመወሰድ ላይ የሚገኙትን እርምጃዎች በመከታተል ላይ ይገኛል። በዚህም መሠረት ኢሰመኮ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ከአጋሮ፣ ከአርባ ምንጭ፣ ከባሕር ዳር፣ ከፍቼ፣ ከጎባ፣ ከሃዋሳ እና ከጅማ ከተሞች መረጃ ማሰባሰብ ችሏል።
ኢሰመኮ የሕክምና ባለሙያዎችን በመወከል የቀረቡለትን ከተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ከጥቅማጥቅም፣ ከሙያ እድገት ዕድሎች እንዲሁም ከምቹ የሥራ ቦታ እና የሥራ ቦታ ነጻነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጤና ሚኒስቴር ያቀረቡ መሆኑን እና መንግሥት እነዚህን ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎች በተሰጠው 30 ቀናት አልፈጸመም በሚል ከግንቦት 5 ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለመረዳት ችሏል።
ኢሰመኮ ጉዳዩን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር ኃላፊዎች፣ ከጤና ባለሙያዎች ተወካዮች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይቶችን ያካሄደ ሲሆን ከፊል እና ሙሉ የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ በአዲስ አበባ ክትትል ባደረገባቸው የጥቁር አንበሳ፣ የቅዱስ ጳውሎስ፣ የቅዱስ ጴጥሮስ እና የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች ኃላፊዎች በማነጋገር መረጃዎችን አሰባስቧል። በዚህም መሠረት በአንዳንድ የሕክምና ተቋማት በጽኑ ሕሙማን ማዕከል የሚገኙ ታማሚዎችን ጨምሮ በሐኪሞች እጥረት ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸውን፤ ከክልል ከተሞች ረጅም ቀጠሮ ጠብቀው ለሕክምና የመጡ ታካሚዎች ለእንግልት የተዳረጉ መሆኑን፤ በባለሙያዎች እጥረት ምክንያት አንዳንድ የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎችን ለረጅም ፈረቃዎች እንዲሠሩ ለመመደብ የተገደዱ መሆኑን እንዲሁም ታካሚዎች ሕክምና ለማግኘት ለረጅም ሰዓታት እንደሚጠብቁ ለማረጋገጥ ተችሏል።
በሌላ በኩል ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳ አድርገዋል፤ በሌሎች በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰዋል ያላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ያዋለ መሆኑን ኢሰመኮ ለመረዳት የቻለ ሲሆን በቁጥጥር ሥር የዋሉ የሕክምና ባለሙያዎች አያያዝን አስመልክቶም ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በጤናው ዘርፍ የሚደረግ የሥራ ማቆም አድማ በማኅበረሰቡ የጤና እና በሕይወት የመኖር መብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ግልጽ እና አሳታፊ በሆነ መንገድ መፍትሔ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲያመቻች እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎችም የኅብረተሰቡን የጤና እና በሕይወት የመኖር መብቶችን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ከሥራ ማቆም አድማው ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ አስተዳደራዊ እና ሌሎች ማናቸውም እርምጃዎች አግባብነት ያላቸውን ሕጎች እና የሰብአዊ መብቶች መርሖችን የተከተሉ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተጨማሪም ኢሰመኮ ከመደበኛው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማነጋገር ጉዳዩ በውይይት እንዲፈታ የሚያደርገውን ጥረት የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።