የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በ156 ፖሊስ ጣቢያዎች እና ኢመደበኛ ማቆያዎች የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስከረም 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል። በውይይቱ ከጨፌ ኦሮሚያ፣ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ መምሪያዎች እና ጣቢያዎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።


በመድረኩ ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ሰዎች መሠረታዊ መረጃዎች መመዝገባቸው፤ ሃይማኖትን፣ ብሔርን፣ የፖለቲካ አመለካከትን እና ሌሎች ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ እስሮች አለመኖር፤ ስልታዊ የሆነ ድብደባ በተጠርጣሪዎች ላይ የማይፈጸም መሆኑ፤ ተጠርጣሪዎች በቤተሰቦቻቸው፣ በጠበቆቻቸው እና በሌሎች ዘመዶቻቸው እንዳይጎበኙ ክልከላ አለመደረጉ፤ የአዳዲስ ማቆያ ክፍሎች ግንባታ እና ነባር ክፍሎችን የማደስ ሂደት መኖሩ እንዲሁም በተወሰኑ የወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች ዐቅም ለሌላቸው ተጠርጣሪዎች የምግብ አቅርቦት መጀመሩ በተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖች መሆናቸው ተገልጿል።


በሌላ በኩል በፖሊስ ጣቢያዎች እና በኢመደበኛ ማቆያ ቦታዎች “ወቅታዊ ጉዳይ” በሚል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እና ክስ ሳይመሠረትባቸው ለተራዘመ እስር የተዳረጉ ተጠርጣሪዎች መገኘታቸው፤ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በተጠርጣሪዎች ምትክ የቤተሰብ አባላት የሚታሰሩ መሆናቸው፤ በፍርድ ቤት ውሳኔ ነጻ የተባሉ ሰዎችን “ወቅታዊ ሁኔታ” በሚል አስሮ የማቆየት ተግባር መኖሩ፤ በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ መታሰራቸው፤ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ እና በምርመራ ወቅት ዛቻ፣ ማስፈራራት እና ድብደባ መፈጸሙ፤ ከአካባቢያቸው ርቀው የታሰሩ ተጠርጣሪዎች ለምግብ እጦት መዳረጋቸው እና ገዝተው ለመጠቀም ምግብ ቤቶች በአቅራቢያ አለመኖራቸው በተግዳሮትነት ተጠቅሰዋል።



በተጨማሪ የመጠጥና የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ ችግር መኖሩ፣ ማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁ፣ በቂ አየርና ብርሃን የማያስገቡ፣ ተባይ ያላባቸው፣ ፍራሽና የሌሊት አልባሳት የሌላቸው መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ተጠርጣሪዎች ሲታመሙ የሕክምና አገልግሎት የማያገኙ መሆኑ፤ ወደ ሕክምና መስጫ ማእከላት ለመሄድ ለአጃቢ ፖሊስ ከ500 እስከ1000 ብር እንዲከፍሉ መገደዳቸው፤ ተጠርጣሪዎችን በዕድሜ እና በሌሎች በሕግ በተቀመጡ ሁኔታዎች መሠረት ለያይቶ ለመያዝ በቂ የማቆያ ስፍራ አለመኖር እንዲሁም በቁጥጥር ሥር ውለው ከሚገኙ እናቶች ጋር ለሚኖሩ ሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን ተጠርጣሪዎች ሁኔታቸውን ያገናዘበ አገልግሎት አለመኖር በአሳሳቢነት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ ያቀረበው የክትትል ሪፖርት በክልሉ የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችን እና ኢመደበኛ ማቆያ ስፍራዎችን ነባራዊ ሁኔታ ያሳየ መሆኑን ገልጸው በተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ረገድ ለተስተዋሉ ክፍተቶች መነሻ ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች እና ሊወሰዱ በሚችሉ የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ተወያይተዋል። በቀጣይ ትኩረት ለሚሹ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት እና በኢሰመኮ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘሪሁን ዱጉማ ኢሰመኮ በየዓመቱ የሚያቀርባቸው የክትትል ሪፖርቶች ለተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች መከበር የፖሊስ ተቋማት ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ጠቃሚ ግብዓት መሆናቸውን በመጠቆም፣ “ክፍተቶች እንዲታረሙ እንሠራለን” ብለዋል። በውይይቱ መጨረሻ የምክረ ሐሳቦች ማስፈጸሚያ የድርጊት መርኃ ግብር በኢሰመኮ እና በተሳታፊዎች በጋራ ተዘጋጅቷል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ተጠባባቂ ከፍተኛ ዳይሬክተር በዳሳ ለሜሳ በተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ተቀራርቦ መሥራት ወሳኝ መሆኑን አስታውሰው፤ ኢሰመኮ በዚህ ረገድ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።