የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመጋቢት እና በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ እና ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ተፈናቅለው በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እና ሀበሽጌ ወረዳ ዳርጌ ከተማ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ከኅዳር 16 እስከ 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ባከናወነው ክትትል፣ በለያቸው ግኝቶች እና ባቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል። በውይይቱ ኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ባከናወነው ክትትል የለያቸው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበዋል። በዚህም መሠረት ከአመያ እና ኖኖ ወረዳዎች ወደ ወልቂጤ ከተማ እና ሀበሽጌ ወረዳ የተፈናቀሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባ አለመደረጉ፣ ተፈናቃዮች መብቶቻቸውን ለመጠቀም የሚያስችሉ ሰነዶች አለማግኘታቸው፣ የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት ያለባቸው መሆኑ፣ የሰብአዊ ድጋፍ እና መሠረታዊ አገልግሎትን ጨምሮ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተፈናቃዮች የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖሩ እንዲሁም የዘላቂ መፍትሔ አማራጮችን የማፈላልግ ሥራ በመንግሥት በኩል አለመጀመሩ ተገልጿል።

ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው፣ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የቢሮ ኃላፊዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተ ኢሰመኮ ያቀረባቸውን ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ተቀብለው በቀጣይ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም ክልሉ የተፈናቃዮች የቀድሞ መኖሪያ ከሚገኝበት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንዲሁም ኢሰመኮን ጨምሮ ከሌሎችም ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ እንደሚሠራ ተገልጿል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም. የተፈናቃዮች ምዝገባ በማከናወን ጊዜያዊ መታወቂያ እንደሚሰጥ፣ አፋጣኝ ምላሽ ለሚያሻቸው ጉዳዮች መፍትሔ እንደሚሰጥ፣ ተፈናቃይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲሁም እናቶች እና ሕፃናት ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ምሕረተአብ ገብረመስቀል፣ የኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የስደተኞች እና የፍልሰተኞች መብቶች ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባ ከማከናወን እና ተገቢ ሰነዶችን ከመስጠት ጎን ለጎን ሰብአዊ ድጋፍና መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ብሎም በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝቧል። ኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበሩ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ውትወታ አጠናክሮ ይቀጥላል።