የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መጪውን 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን በተመለከተ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ጥቅምት 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሁለትዮሽ ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና አባላቱ ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ኢሰመኮ በ6ኛው ዙር ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ፣ የማሟያ እና ድጋሚ ምርጫዎች ላይ ባካሄዳቸው ክትትሎች ያስተዋላቸው የሰብአዊ መብቶች እክሎች በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዳይደገሙ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አመላክቷል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በመወከል በሁለትዮሽ ውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች የኢሰመኮን ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ተቀባይነት ገልጸው፣ ቦርዱ ከ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን በዝርዝር አስረድተዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ(Geographical Information System GIS) ጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት በመታገዝ የምርጫ ጣቢያዎችን በመለየት ለታዛቢዎች ተደራሽ የማድረግ አሠራር መዘርጋቱን፣ 8 ተጨማሪ ጽሕፈት ቤቶችን በማቋቋም የጽሕፈት ቤቶቹን ብዛት ወደ 22 ከፍ ማድረጉን፣ ኢሰመኮ በሕግ የተሰጠው ምርጫን የመከታተል ሥልጣን ለመተግበር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በተመለከተ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል በቂ ግንዛቤ መፈጠሩ፣ መራጮችና እጩዎች ባሉበት ቦታ ሆነው መመዝገብ የሚችሉበት ተደራሽ የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት መዘጋጀቱ፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ በተለይም ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሲቪል ማኅበራት ነጻ ተሳትፎ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በማጤን ቦርዱ ሥጋቱን ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁ ተገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያደረገ ያለው ዝግጅት እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሠራ መገኘቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ በምርጫ ወቅት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ነጻ ተሳትፎ በማረጋገጥ ረገድ በተለይም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ጋር በተያያዘ ኢሰመኮ ተከታታይ ውትወታ እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። ቦርዱ ምርጫውን በአግባቡ ማከናወን እንዲችል የሚስተዋለውን የበጀት እና የተሽከርካሪ እጥረት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል። አክለውም ኢሰመኮ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለሚያከናውነው የምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል።