የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ታኅሣሥ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል ጉብኝት አድርገዋል። በማእከሉ የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ በታዩ መልካም ለውጦች እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ከተጠርጣሪዎች ተወካዮች፣ ከማእከሉ እና ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡


ተጠርጣሪዎች በማእከሉ ስለሚኖራቸው ቆይታ እና ስለሚያገኟቸው አገልግሎቶች በቂ ማብራሪያ የሚሰጣቸው መሆኑ፣ መብቶች እና ግዴታዎቻቸውን በጽሑፍ እንዲያገኙ መደረጉ፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ፣ ለሃይማኖት ነጻነት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ፣ በማእከሉ መሠረታዊ ፍጆታዎችን በግዢ ማግኘት የሚቻልበት አማራጭ መቅረቡ እና ለመጠጥና ንጽሕና መጠበቂያ የሚሆን በቂ የውሃ አቅርቦት መኖሩ ኢሰመኮ በጉብኝቱ አበረታች ሆነው ካገኛቸው ሁኔታዎች መካከል ናቸው።






በሌላ በኩል ማእከሉ መያዝ ከሚችለው የተጠርጣሪዎች ቁጥር በላይ የያዘ በመሆኑ ከፍተኛ መጨናነቅ መፈጠሩ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ተጠርጣሪዎች ከሌሎች ተለይተው አለመያዛቸው፣ መዝጊያ የሌላቸው መጸዳጃ እና መታጠቢያ ቤቶችን ጨምሮ የተወሰኑ የውሃ ቧንቧዎች አገልግሎት ያቆሙ መሆናቸው፣ በማረሚያ ቤቱ የተወሰኑ ዞኖች ለተጠርጣሪዎች በቂ የመንቀሳቀሻ ቦታ አለመኖሩ፣ ተጠርጣሪዎች ለመያዝ የሚፈቀድላቸው አነስተኛ የብር መጠን (እስከ 200 ብር ብቻ) መሆኑ የሚያስፈልጓቸውን ሸቀጦች ለመግዛት በቂ አለመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች የሚፈልጓቸውን መጻሕፍት ለማስገባት መቸገራቸው እንዲሁም ለአንድ ተጠርጣሪ የእለት ቀለብ የተመደበው 35 ብር ምግብ ለማቅረብ በቂ አለመሆኑ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ኢሰመኮ በጉብኝቱ ለመገንዘብ ችሏል፡፡






የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና የቂሊንጦ ጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል የሥራ ኃላፊዎች የአሁኑን ጉብኝት ጨምሮ ኢሰመኮ በየጊዜው የሚያካሂዳቸው የክትትልና ውትወታ ተግባራት የተጠርጣሪዎችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል ጠቃሚ ግብአት እንደሚሆናቸው በመጠቆም ተቋማቱ ተቀራርበው መሥራታቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።


በተጨማሪም መጨናነቅን ለማስቀረት ፍርድ የተሰጣቸውን ሰዎች ወደ ቃሊቲ ከፍተኛ ማረሚያ ተቋም ለማዛወር በማረሚያ ቤቱ የተወሰነ መሆኑን፤ የታራሚዎች የእለት በጀት የሚሻሻልበትን ሁኔታ በተመለከተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሚገኙ እንዲሁም ተጠርጣሪዎች በቆይታቸው ለመሠረታዊ ፍላጎት ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ሊያደርጉ የሚችሉበትን ሥርዓት ለመፍጠር ከባንኮች ጋር እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ፍርድ የተሰጣቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ለማዛወር የተላለፈው ውሳኔ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በማእከሉ ለሚገኙ የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች የተመደበው በጀት እንዲሻሻል ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ እንዲሁም ከንጽሕናና ሌሎች አገልግሎቶች መሠረተ ልማት መሟላት ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡