የኢትዮጲያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) 7ተኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን በተመለከተ በሚያዚያ 12 እና 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል። ስልጠናው በምርጫ ክትትል ሥራ ላይ ለሚሳተፉ የኢሰመኮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የሰብአዊ መብት ባለሞያዎች የተዘጋጀ ነው።


ኢሰመኮ በተሻሻለው ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1224/2012 አንቀጽ 6 (11) መሠረት በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅን የመከታተል ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ነው። ይህ ስልጠናም ተሳታፊዎች በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ላይ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ለማጎልበት፣ ቀደም ሲል ከተከናወኑ የምርጫ ክትትሎች ከተገኙ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ትምህርት ለመውሰድ፣ እንዲሁም በክትትል ስልቶች ላይ ወጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።
በሥልጠናው ወቅት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ-ምርጫ፣ የምርጫ ዕለት እና ድህረ-ምርጫ ሂደቶች ላይ ኢሰመኮ የሚኖረውን ሚና የሚዳስስ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀው የኢሰመኮ ስትራቴጂ መሠረት እስካሁን የተከናወኑ እና በቀጣይ ለመተግበር የታቀዱ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።



በተጨማሪም በምርጫ ወቅት በስፋት ከሚነሱት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶች እንዲሁም ሌሎች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያጋጠሙ ግኝቶች ላይ ውይይት ተደርጓል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢሰመኮ ቀደም ሲል ካከናወናቸው የምርጫ ክትትሎች ያገኛቸውን ልምዶች፣ በሥራ ላይ የሚውሉ የክትትል ዘዴዎችን እና የክትትል ሥራውን ለማሳለጥ የተዘጋጀውን የሞባይል መተግበሪያ (Application) በተመለከተ በከፍተኛ ባለሙያዎች የቀረቡ የመወያያ ጽሑፎችና የተግባር ማሳያዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
በሥልጠናው ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕግ አማካሪ አይተነው ደበበ፤ አጠቃላይ የምርጫ ሂደትን፣ የቦርዱን አሠራርና ኃላፊነቶች እንዲሁም የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች የሥነ-ምግባር መመሪያን የሚያብራራ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዳይሬክተር መቅደስ አመኑ፤ ኢሰመኮ የምርጫውን ሂደት በቅርበት በመከታተል የሰብአዊ መብቶች የተከበሩበት እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ገልጸው ይህ ሥልጠና የዚሁ የክትትል ሥራ የቅድመ-ዝግጅት አካል መሆኑን አስረድተዋል።