በኢትዮጵያ ለሚከናወነው የሽግግር ፍትህ ትግበራ ስኬት የማህበረሰብ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። እነዚህ በማህበረሰቡ ዘንድ ባላቸው ከፍተኛ ተቀባይነት እና የሞራል የበላይነት ምክንያት በግጭት የተጎዱ ወገኖችን በማቀራረብ፣ እውነትን በማውጣት፣ ይቅርታን እና እርቅን በማውረድ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ሊያበረክቱ ይችላሉ። በተጨማሪም ግፍ እና በደል የደረሰባቸው ወገኖች ብሶታቸውን በነፃነት እንዲናገሩ ደህንነታቸው የተጠበቀ መድረክ ከመፍጠር ባለፈ፣ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ በግልፅነት እና በፍትሃዊነት እንዲመራ በማድረግ በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምና እውነተኛ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር መሰረት ይጥላሉ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ይህንኑ በውል በመገንዘብ በኢትዮጵያ በሚተገበረው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ጉልህ ሚና ለማጠናከር ያለመ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል። በዚህም በበደሌ እና ይርጋለም ከተሞች ስልጠናውን በተከታታይ አካሂዶ አጠናቋል።

በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጁት እነዚህ ስልጠናዎች፣ ከመስከረም 04 እስከ 09 ቀን 2019 ዓ.ም. በበደሌ ከተማ ለቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባቦር፣ ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም በይርጋለም ከተማ ከሲዳማ ክልል ምስራቃዊ፣ ደቡባዊ፣ ማዕከላዊ እና ሰሜናዊ ዞኖች ለተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሀገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ መሪዎች ተሰጥተዋል።

ስልጠናዎቹ ተሳታፊዎች ስለ ሰብአዊ መብቶችና የሽግግር ፍትሕ ምንነት፣ አስፈላጊነትና ግቦች ያላቸውን እውቀት ለማሳደግ፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ባሉ የሽግግር ፍትሕ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ እንዲሁም የማኅበረሰብ መሪዎች በሂደቱ ላይ ያላቸውን ቁልፍ ሚና እንዲረዱና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ያለሙ ነበሩ።

በአጠቃላይ ከስምንት ዞኖች ለተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ መሪዎች የተሰጡት እነዚህ ስልጠናዎች፣ በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ መካከል ስላለው ጥብቅ ቁርኝት፣ የጥሰቶች ሰለባ የሆኑ አካላትን መብት ስለማስከበር፣ እና የማኅበረሰብ ደረጃ ዕርቅን ስለማመቻቸት ሰፊ ውይይት እንዲደረግ አስችለዋል።

ኮሚሽኑ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በባህላዊና ሃይማኖታዊ የዕርቅ ሥርዓቶች ላይ ያላቸው ጥልቅ ልምድ፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ በሰብአዊ መብቶች መርሆች ላይ ተመስርቶ ፍትሐዊና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በማመን፣ ተመሳሳይ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ለሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ለማስፋትም አቅዷል።