የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን (ACHPR) እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በግዳጅ ወይም ያለፈቃድ መሰወር ጉዳዮች የሥራ ቡድን (WGEID) ጋር በመተባበር ነሐሴ 25 ቀን 2018ዓ.ም ውይይት አካሂዷል። ዝግጅቱ ከመንግስት አካላት፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከልማት አጋሮች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮችን አሰባስቧል።




የውይይቱ ዋና ዓላማ ባለድርሻ አካላት ስለ አስገድዶ መሰወር ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እና በየዓመቱ ነሐሴ 24 የሚከበረውን የአስገድዶ መሰወር ሰለባዎች ዓለም አቀፍ ቀንን ማስታወስ ነበር። በውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች ከአስገድዶ መሰወር የመጠበቅ ዓለም አቀፍ ስምምነትን (ICPPED) እና የአፍሪካ ኮሚሽን በ2014 ያወጣውን በአስገድዶ መሰወር ላይ የተዘጋጀ መመሪያን ጨምሮ ቁልፍ ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ማዕቀፎችን ተመልክተዋል። በውይይቱ ወቅት ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሀገር ውስጥ ውትወታውን ለማጠናከር ተግባራዊ ግንዛቤዎችን አካፍለዋል፣ እንዲሁም የተመድ WGEID እና የአፍሪካ ኮሚሽን በሞት ቅጣት፣ ከፍርድ ውጪ እስርን፣ ያለአግባብ ግድያ እና በአፍሪካ አስገድዶ መሰወር ላይ ያለውን የሥራ ቡድን ተልእኮ አቅርበዋል። በተጨማሪም ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር የመጠበቅ ዓለም አቀፍ ስምምነትን (ICPPED) ማጽደቋ ያለውን አስፈላጊነት አብራርተዋል።





የአፍሪካ ኮሚሽን ሊቀመንበር እና የኮሚሽኑ በሞት ቅጣት፣ ከፍርድ ውጪ እስርን፣ ያለአግባብ ግድያ እና በአፍሪካ የአስገድዶ መሰወር ላይ የሥራ ቡድን ሊቀመንበር ኢድሪሳ ሶው፣ አስገድዶ መሰወርን “አዋራጅ ወንጀል” ሲሉ ገልጸውታል። ይህን እጅግ አደገኛ የሚያደርገው ተጠቂውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት አካል ወንጀሉን በመፈጸም ውስጥ መሳተፉ እንደሆነ አጠንክረው ገልጸዋል። ኢድሪሳ ሶው በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለውን የሽግግር ፍትህ ሂደት በመጥቀስ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ጠንካራ ትብብር እንዲገነቡ፣ የሕግ ጥበቃዎችን እንዲያጠናክሩ እና ሀገሪቱ ICPPED ልታፀድቅ የምትችልበትን እድል እንዲደግፉ አሳስበዋል።





የተመድ WGEID አባል የሆኑት ዶ/ር አዋ ባልዴ፣ የመታሰቢያ ቀኑ ከሁሉም በላይ ስቃያቸው ብዙ ገፅታ ያለው እና ብዙ ጊዜም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ለሆኑ ሰለባዎች የተዘጋጀ ቀን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ስለ አስገድዶ መሰወር መሰረታዊ ባህርያት እንዲሁም የሥራ ቡድኑ ተልእኮ እና የሥራ ዘዴዎች ማብራሪያ ለተሳታፊዎች ሰጥተዋል፤ ይህም የሀገር ጉብኝቶችን ማድረግ፣ ለሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት ማቅረብ፣ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችን መከታተል እና የሰብአዊ ተልእኮውን መወጣት ያካትታል። በተጨማሪም ዶ/ር ባልዴ የሥራ ቡድኑ በአፍሪካ እና በመላው ዓለም ላሉ የጠፉ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ያለውን አጋርነት እንደገና አረጋግጠዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ፣ አስገድዶ መሰወርን መከልከል የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ሕግ ዋና መሰረት በመሆኑ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር የመጠበቅ ዓለም አቀፍ ስምምነትን ማጽደቅ ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፉን የበለጠ የሚያጠናክር እና ለመከላከል፣ ለምርመራ፣ ተጠያቂነት እና ለሰለባዎችና ቤተሰቦቻቸው ካሳ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አስታውሰዋል። “ይህ መታሰቢያ ከተጎጂዎች ቤተሰቦችና ማህበረሰቦች ጎን መቆምን የሚያስችል እና ማንም ሰው ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዳይሆን ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ይሆናል” ብለዋል።
ውይይቱ ተሳታፊዎች ሁሉ አስገድዶ መሰወርን በመከላከል፣ ለሰለባዎች ፍትህ እና ካሳ በማረጋገጥ እንዲሁም ጠንካራ ሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሕግ ጥበቃዎችን በመዘርጋት የየራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሚያሳስብ የጋራ ጥሪ በማቅረብ ተጠናቅቋል።