የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ከኢትዮጲያ አሠሪዎች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ኅዳር 3 ቀን 2019 ዓ.ም. የዐቅም ግንባታ ዐውደ ጥናት አዲስ አበባ በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት አካሂዷል። ዐውደ ጥናቱ የኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ ተወካዮችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ስለ ዓለም አቀፍ የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መሥፈርቶች ያላቸውን ግንዛቤ ለማጠናከር እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት አዳዲስ የሕግ ማዕቀፎች በኢትዮጵያ የንግድ ተቋማት እና በሰብአዊ መብቶች አሠራር ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንደምታ ለመፈተሽ ያለመ ነው። 

በዐውደ ጥናቱ መክፈቻ የሮያል ዴንማርክ ኤምባሲ ተቀዳሚ ጸሐፊ ክርስቲያን ዌስታድ በንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ዐቅምን ማሳደግ ያለውን ፋይዳ እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን ማክበርና ለሰብአዊ መብቶች ተገቢ ትጋት የሚያደርግ የንግድ አሠራርን መተግበር ለንግድ ተቋማት ያለውን ጠቀሜታ አጽንዖት ሰጥተው አብራርተዋል። የኢትዮጵያ አሠሪዎች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ዳዊት ሞገስ በበኩላቸው፤ የንግድ ተቋማት የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ለመፍታት እና ለአዳዲስ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እውቀት እና የአሠራር ሥርዓት እንዲኖራቸው ማስቻል ያለውን አፈላጊነት ገልጸዋል።   

በኢሰመኮ እና በዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ከፍተኛ ባለሙያዎች በንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያሉ ዋና ዋና ጽንሰ ሐሳቦችና መሥፈርቶች የተዳሰሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች (United Nations Guiding Principles on Business and Human Rights (UNGPs))፣ የሰብአዊ መብቶች ተገቢ ጥንቃቄ (Human Rights Due Diligence)፣ እንዲሁም የቅርብ ጊዜው የአውሮፓ ኅብረት የሕግ እና የቁጥጥር ማዕቀፎች፣ በተለይም የኮርፖሬት የዘላቂነት ተገቢ ትጋት መመሪያ (Corporate Sustainability Due Diligence Directive (CSDDD))፣ የአውሮፓ ኅብረት የግዳጅ ሥራን የሚከለክለው ደንብ እና የደን መጨፍጨፍ መከላከል ደንብ (EU Forced Labour Regulation, and the EU Deforestation Regulation) ይገኙበታል። 

የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ  እንዲሁም ኢሰመኮ ለሰብአዊ መብቶች ተገቢ ትጋት የሚያደርግ የንግድ አሠራር እንዲሰፍን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ላይ ተወያይተዋል። 

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ጉዳዮች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሐዊ አስፋው ዐውደ ጥናቱ ኢሰመኮ ለሰብአዊ መብቶች ተገቢ ትጋት የሚያደርግ የንግድ አሠራር እንዲስፋፋ እና የሀገር ውስጥ የንግድ  አሠራሮች ከዓለም አቀፍ  የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎች  ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ለማስቻል እያደረገ ያለው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብርና ለዘላቂ ልማት አስተዋጽዖ የሚያበረክት የንግድ አሠራር እንዲጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።