የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአካል ጉዳተኞች የተሐድሶ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቀደም ሲል የተሰጡ ምክረ-ሐሳቦችን አፈጻጸም ክትትል እና ግምገማ አካሂዷል።
የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሃመድ አሕመድ አካል ጉዳተኞች የተሐድሶ አገልግሎት የማግኘት መብት ላይ በተደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ምክረ-ሐሳቦች አፈጻጸም ለመገምገም ከደቡብ ኢትዩጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በጅንካ ከተማ ውይይት አድርገዋል።


በተጨማሪም ከአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች የአካል ተሐድሶ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ እንዲሁም የማዕከሉን እና የዊልቸር ማምረቻውን አሁናዊ ሁኔታ ተመልክተዋል።
በጉብኝቱና በውይይቱ ማዕከሉ ክራንች እና ነጭ በትር ማምረት መጀመሩ፣ የሕፃናት የዞረ እግር ህክምና ክፍል ታድሶ ሥራ መጀመሩ፣ የፊዚዮቴራፒ ማሽኖች ጥገና እየተከናወነ መሆኑ እና የቦርሳ፣ ቀበቶና ጫማ ማምረት መጀመሩ ከተለዩ አወንታዊ አፈጻጸሞች መካከል ናቸው።


ይሁን እንጂ በዘርፉ ስልጠና የሚሰጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ባለመኖሩ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩ፣ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎች ዝቅተኛ መሆናቸው እና አገልግሎቶች በከተሞች ብቻ ተከማችተው በገጠር የሚገኙ ዜጎች እየተቸገሩ እንንሚገኙ መታየቱ በዋና ክፍተትነት የተለዩ ናቸው።
በአጠቃላይ ጥራት ያለውና ተመጣጣኝ አገልግሎት ለመስጠት በፖሊሲ፣ በፋይናንስ፣ በመሣሪያ አቅርቦትና በተደራሽነት ዙሪያ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸው ተመልክቷል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር፤ በዘርፉ የታዩትን በጎ ጅምሮች በማስቀጠል እና ያሉትን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም በቂና ቀጣይነት ያለው የበጀት ድልድል እንዲኖር፣ የተቋማት አደረጃጀት እንዲጠናከር እና በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ የትምህርት ፕሮግራሞች በዩኒቨርሲቲዎች እንዲስፋፉ ኢሰመኮ የሚያደርገውን የውትወታ ሥራ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።