የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ለአካል ጉዳተኞች የተሐድሶ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተገነባው ማእከል በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል፡፡ በምክክሩ የሚመለከታቸው የአፋር ክልል ቢሮዎች፣ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና ሌሎች አጋዥ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

EHRC’s expert giving a presentation to the participants
የኢሰመኮ ባለሙያ ለተሳታፊዎች ገለጻ ሲሰጥ

የውይይት እና የውትወታ መድረኩ ኮሚሽኑ በክልሉ የተካሄደው ጦርነት በአካል ጉዳተኞች መብቶች ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ለመገምገም ከየካቲት 8 እስከ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል መሠረት ማእከሉ ያሉበት ችግሮች ተቀርፈው በአስቸኳይ አገልግሎት እንዲጀምር ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ ኢሰመኮ የማእከሉን አገልግሎት መጀመር አስመልክቶ ክትትል ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፣ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ረጅም ጊዜ በመውሰዱ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድ የጋራ መድረክ ለመመካከርና ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ እንዲችሉ በማሰብ መድረኩን አመቻችቷል።

Afar Women and Social Affair Bureau’s representative giving a presentation to the participants
የአፋር ክልል ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካይ ለተሳታፊዎች ገለጻ ሲሰጥ

በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የተሐድሶ አገልግሎት የሚያገኙት በአብዛኛው በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ ከተማ ወደሚገኘው የደሴ የአካል ጉዳተኞች ተሐድሶ ማእከል በመሄድ ነው፡፡ ይኹንና በደሴ ከተማ የሚገኘው ማእከል በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጉዳት የደረሰበት በመሆኑና በሁለቱም ክልሎች በተካሄደው በዚሁ ጦርነት ምክንያት የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ቁጥር የጨመረ በመሆኑ አገልግሎቱን እንደ ልብ ማግኘት አዳጋች አድርጎታል፡፡

በምክክሩ ከኢሰመኮ የክትትል ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች በተጨማሪ የአፋር ክልል ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ማእከሉን ለማቋቋም የተደረጉ ጥረቶችን፣ አሁን ላይ የሚገኝበትን ሁኔታ፣ አገልግሎት መስጠት ያልጀመረበትን ምክንያቶችና አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ድጋፎችን አስመልክቶ ዝርዝር ጥናት አቅርቧል፡፡ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ቢሮ ተወካዮችም በክልሉ የተሐድሶ አገልግሎት በማቅረብ ሂደት ውስጥ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች እና በአጭር እና በረጅም ጊዜ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ ሐሳባቸውን አቅርበው ዝርዝር ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ የተሐድሶና የአካል ድጋፍ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች የሚደረግ እርዳታ ወይም ድጋፍ ሳይሆን ሌሎች ሰብአዊ መብቶችን በምልዐት ለመጠቀም የሚያስችል መሠረታዊ ሰብአዊ መብት መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ እና አገልግሎቱን በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች በተቻለ ቅርበት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ በመክፈቻ መልእክታቸው አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል። በምክክሩ ወቅትም ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀችውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ጨምሮ በሌሎችም ብሔራዊ ሕጎች መሠረት መንግሥት የአካል ጉዳተኞች የተሐድሶ እና የማቋቋሚያ አገልግሎቶችን የማደራጀት፣ የማጠናከር እና የማስፋፋት ግዴታ ያለበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ICRC Ethiopia’s representative giving a presentation to the participants
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ ተወካይ ለተሳታፊዎች ገለጻ ሲሰጥ

በመጨረሻም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአጭር እና በረጅም ጊዜ ሊወጡ የሚችሏቸውን ኃላፊነቶችና ተግባራት በመለየት ማእከሉ በአጠረ ጊዜ አገልገሎት እንዲጀምር ለማድረግ በሚቻልባቸው ነጥቦች ዙሪያ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡