በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ሊጫወቱ የሚገባቸውን ወሳኝ ሚና አስመልክቶ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች የተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሄደ።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሴቶችና ህፃናት መብቶች ኮሚሽነር እንዲሁም የሽግግር ፍትህ እና የፍትህ ተደራሽነት አስተባባሪ ኮሚሽነር አሸነፈች አበበ፤ የብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ከጸደቀ በኋላ ፖሊሲውን ወደ ተግባር ለመተርጎም የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።





ኮሚሽነሯ ተቋማቱ በምርምር፣ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ የታሪክ ትንተና በማድረግ እና በቀጣይነት በሚደረጉ የማህበረሰብ ተሳትፎዎች አማካኝነት ያለፉ ጥሰቶችን በጥልቀት ለመረዳትና የጋራ ታሪካዊ ትውስታን ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የብሔራዊ ፖሊሲውን ዓላማዎችና ቁርጠኝነቶች ወደ መሬት ለማውረድ ተአማኒነት ያለው መረጃ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ወሳኝ በሆነበት በዚህ ወቅት የተደረገው ምክክር ወቅታዊና ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል።





በዕለቱ የመልዕክት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ኤክስኪዮቲቭ ዲን ፕሮፌሰር ሙራዱ አብዶ እና የሽግግር ፍትሕ ጥምረት (TJC) አባል ዶ/ር ታደሰ ስሜ በበኩላቸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፈጸሚዎችን አቅም በመገንባት፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እና የረቂቅ ህጎችን ጥራት ለማሻሻል ግብዓት በመስጠት ረገድ ያላቸውን ኃላፊነት አንስተዋል።
ተቋማቱ ይህንን አደራ ለመወጣት ከኢሰመኮ እና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ያላቸውን ትብብርና ቅንጅት ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።




በውይይቱ ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ መድረኩ የአካዳሚክ አስተዋጽኦዎችን ለመገንዘብ፣ የእውቀትና የምርምር ክፍተቶችን ለመለየት እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት ተግባራዊ የትብብር መስኮችን ለመዘርጋት ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
መድረኩ በኢሰመኮ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት እና በሽግግር ፍትሕ ጥምረት (TJC) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።