- Version
- Download 15
- File Size 2.62 MB
- File Count 1
- Create Date May 10, 2024
- Last Updated May 10, 2024
የ2015 በጀት ዓመት የፖሊስ ጣቢያዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዓመታዊ የክትትል ሪፖርት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች መካከል በፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በመከታተል የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ አንዱ ነው። ለዚህም የክትትልና ምርመራ የሥራ ክፍል፤ በፖሊስ ጣቢያዎች በሚገኙ ተጠርጣሪዎች መብቶች ዙሪያ የሕግ ማዕቀፎች አተገባበርን በተመለከተ የክትትልና ምርመራ እንዲሁም ዘርፈ-ብዙ የውትወታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህ ዓመታዊ ሪፖርት በ2015 በጀት ዓመት በፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ፣ መከበርና መጠበቅ በተመለከተ አበረታች እመርታዎች፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች፣ ማጠቃለያ እና ዝርዝር ምክረ ሐሳቦችን ይዟል። ሪፖርቱ የሚሸፍናቸው አካባቢዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ በአፋር፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በቀድሞው ደ/ብ/ብ/ሕ/ ክልሎች ሲሆን፤ በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች በ2015 በጀት ዓመት በተለያየ ጊዜ የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተገኙ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አግባብነት ካላቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችና መስፈርቶች እንዲሁም ብሔራዊ ሕጎችና የፖሊሲ ማዕቀፎች አንጻር በመተንተን የተዘጋጀ ነው። በፖሊስ ጣቢያዎቹ የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ የተደረገው ክትትል በኮሚሽኑ በተዘጋጀው ማገናዘቢያ ወይም ቼክ ሊስት መሠረት ሲሆን በዚህም በዋነኝነት የተጠርጣሪዎችን አያያዝ ሕጋዊነት፣ የተጠረጠሩበትን ምክንያት ከመነገር፣ ጭካኔ ከተሞላበት ኢ-ሰብአዊና አዋራጅ ቅጣት የመጠበቅ መብት፣ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ፣ በዋስ የመፈታት፣ ቃላቸውን ተገደው ያለመስጠት፣ ያለመናገር/ዝም የማለት መብት፣ በሕግ ባለሙያ ወይም ጠበቃ የመወከል፣ በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት፣ ምግብ፣ ውሃ፣ ሕክምና ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማገኘት እና ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ የመያዝ መብቶች ጉዳዮችን የተመለከተ ነው።