Download
Download is available until [expire_date]
  • Version
  • Download 55
  • File Size 1.36 MB
  • File Count 1
  • Create Date February 6, 2025
  • Last Updated February 6, 2025

የመገናኛ ብዙኃን የቁጥጥር ሥራዎች አተገባበር ከሴቶች ሰብአዊ መብቶች አንጻር (የጥናት ሪፖርት)

መገናኛ ብዙኃን የሚመሩባቸው ሕጎችና ፖሊሲዎች፣ የሚከተሏቸው አሠራሮች እንዲሁም የሚያሰራጯቸው ይዘቶች የሴቶች መብቶች እንዲጠበቁ ወይም በተቃራኒው እንዲሸረሸሩ በማድረግ ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ ነው። መንግሥት የሴቶችን መብቶች ተግባራዊነት ለማረጋገጥ በተለይም ሁሉም መገናኛ ብዙኃን በሴቶች ላይ የሚደርሱ መድልዎ እና አግላይ አስተሳሰቦችን፣ አገላለጾችን፣ አሠራሮችንና ይዘቶችን እንዲያስወግዱ ለማበረታታት ውጤታማ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሴቶች መብቶች ሁኔታዎች እንዲሁም ተዛማጅ ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ጥናት የማድረግና የተለዩ የአፈጻጸም ክፍተቶችም ሆነ ጥሰቶች ውጤታማ ምላሽ እንዲኖር የመሥራት ኃላፊነቱን ተከትሎ የመገናኛ ብዙኃን የቁጥጥር ሥራዎች ከሴቶች መብቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ለመለየት በሁለት ዙር መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ አከናውኗል፡፡ በመጀመሪያ ዙር ከታኀሣሥ 1 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዲሁም በሁለተኛ ዙር ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የብሮድካስት ተቋማት (ቴሌቪዥንና ሬዲዮ) እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት መረጃዎችን አሰባስቧል። በተጨማሪም የጥናቱን ረቂቅ ሪፖርት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ ላይ በማቅረብ ተጨማሪ ግብዓቶች እንዲካተቱ አድርጓል።

በመገናኛ ብዙኃን በተለይም በቴሊቪዥን ፕሮግራሞች ሴቶች የሚገለጹበት እና የሚሳሉበት መንገድ (women’s portrayal) እንዲሁም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በተመለከተ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ዙሪያ ዙሪያ ኢሰመኮ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ሰብአዊ መብቶችን የማስጠበቅ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ግዴታውን እየተወጣ ያለበትን አግባብ ለመረዳት የተጠኑ በቂ ጥናቶች ባለመኖራቸው ምክንያት ይህንን ጥናት ማከናወን አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። የጥናቱ ዋና ዓላማ የመገናኛ ብዙኃን የቁጥጥር ሥራዎችን አተገባበር ከሴቶች መብቶች አንጻር በመመርመር ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ ሲሆን በጥናቱ በተለዩ ክፍተቶች መሠረት እንደ አስፈላጊነቱ ክትትልና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውትወታ ይከናወናል። በተለይም ሴቶች በብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን የሚገለጹበት እና የሚሳሉበት መንገድ፣ ትርጉም ያለው ውክልናና ተሳትፎ (ለምሳሌ ሴቶች እንደ ባለሞያ፣ አመራርና ውሳኔ ሰጪ፣ ሴቶች እንደ መረጃ ምንጭ ወዘተ.) እንዲሁም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በተመለከተ የሚቀርቡ ዝግጅቶች በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉበት መንገድ ላይ ያለው የቁጥጥር ሥራ ምን ይመስላል የሚለውን ለመረዳት የሚያግዝ ጥናት ነው።