የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዘላቂ መፍትሔዎች ቀጠናዊ ሴክሬታሪያት (The Regional Durable Solutions Secretariat (ReDSS)) ጋር በመተባበር ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ አተገባበርን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና አባላት፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተፈናቃዮች ከሚያስተናግዱ ክልሎች የተወከሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በመድረኩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ጥበቃን እና ድጋፍን የተመለከቱ የፖሊሲ፣ የሕግ እና ተቋማዊ ማዕቀፎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ ብሔራዊ ሕግ ይዘትና ያለበት ደረጃ፣ የኢሰመኮ የክትትል ግኝቶች፣ ዘላቂ መፍትሔ የማፈላለግ ተግባራት ያሉበት ሁኔታ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰተዋሉ አሳሳቢ ጉዳዮችና ምክረ ሐሳቦች፣ የዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ብሔራዊ ስትራቴጂ ከተዘጋጀበት ጊዜ ጀምሮ የተከናወኑ ተግባራት፣ የታዩ ለውጦች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ኃላፊነቶችን የተመለከቱ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት ሂደት መንግሥት መር እና በመቀናጀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ አጽንዖት የተሰጠው መሆኑ፣ ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ሂደት የተገኙ ስኬቶች፣ በብሔራዊ ስትራቴጂው ትኩረት የተሰጣቸው እና በትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የተመለከቱ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። የአፋር፣ የአማራ፣ የሶማሊ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የትግራይ ክልሎች ተሳታፊዎችም ብሔራዊ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራት እና በአፈጻጸም ወቅት የገጠሟቸው ተግዳሮቶች፣ መልካም አጋጣሚዎች እንዲሁም በቀጣይነት ለማከናወን ስለዐቀዷቸው ተግባራት ያላቸውን ልምድ አጋርተዋል።

እንጉዳይ መስቀሌ፣ የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች ሰብአዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የካምፓላ ስምምነትን ተቀብላ ያጸደቀች ሀገር እንደመሆኗ ስምምነቱ በሚጠይቀው መሠረት ማስፈጸሚያ ብሔራዊ ሕግ እና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖር ማድረግ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች አጠባበቅ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያግዝ መሆኑ፣ ዘላቂ መፍትሔ ከማፈላለግ ተግባር እኩል ለመፈናቀል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ የመፈለግ አስፈላጊነት፣ የልማት ሥራዎች እንዲሁም በሂደቱ በባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

የተከበሩ እውነቱ አለነ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ እውነቱ አለነ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በሚመለከት ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ሲያከናውናቸው በነበሩ ሥራዎች ላይ የታዩ መልካም ጎኖች እና ክፍተቶችን ገልጸው፤ የሀገር ውስጥ መፈናቀልን መከላከል እንዲሁም ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ እና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ብርሃኑ አዴሎ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኢሰመኮ የተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እና የዘላቂ መፍትሔ አተገባበርን በተመለከተ በቂ ክትትል በማድረግ እና ምክረ ሐሳብ በመስጠት ላለፉት ዓመታት የሰብአዊ መብቶቻቸው አያያዝ እንዲሻሻል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን የመወትወት ሥራዎች እያከናወነ መቆየቱን ገልጸዋል አክለውም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም እና ዘላቂ መፍትሔ የመስጠት ሥራ የባለድርሻ አካላትን ተግባር ተኮር ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።