ሕፃን ወታደሮች፣ ሕፃናትን በጦርነት ወይም በግጭት ውስጥ ማሳተፍ ምን ማለት ነው?
ዓለም አቀፉ የሕፃናት መብቶች ስምምነት፣ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደኀንነት ቻርተር እንዲሁም ሕፃናትን በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ ማሳተፍን በተመለከተ የወጣው ዓለም አቀፉ የሕፃናት መብቶች ስምምነት አማራጭ ፕሮቶኮል (Optional Protocol to the Convention on the Rights of the Child on the Involvement of Children in Armed Conflict) ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ሕፃን እንደሚባል ይደነግጋሉ። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሕፃናትን የዕድሜ ወሰን በግልጽ ባያስቀምጥም እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀች በመሆኗ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) መሠረት የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው። ስለሆነም በኢትዮጵያም ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ሕፃን ይባላል።
ሕፃን ወታደሮችን የሚመለከቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶችና ሕጎች ቢኖሩም ሕፃን ወታደሮች ማለት ምን ማለት ነው ለሚለው ግን ትርጉም አይሰጡም፡፡ ከጦር ኃይሎች ወይም ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ተሳትፎ ያላቸውን ሕፃናት አስመልክቶ የወጣው የፓሪስ መርሖዎችና መመሪያዎች፣ ሕፃናት ወታደሮች ወይም ሕፃናትን በጦርነት ወይም በግጭት ውስጥ ማሳተፍ ማለት አንድን ሕፃን በመከላከያ ወይም በታጠቁ ቡድኖች በማናቸውም መንገድ ለውትድርና አገልግሎት መመልመልን ወይም በምግብ አብሳይነት ወይም አቅራቢነት፣ በሰላይነት፣ በመልዕክተኛነት፣ በወሲብ ብዝበዛ ድርጊት እና በሌሎች መሰል ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ማድረግን እንደሚያጠቃልል ያስቀምጣል፡፡ ይህም የሚገልጸው በግጭት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውን ብቻ ሳይሆን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸውንም ሕፃናት እንደሚያካትት ነው።
ተፈጻሚነት ያላቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሕግ ማዕቀፎች የትኞቹ ናቸው?
ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች
ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ስምምነት የሕፃናት መብቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደነግግ ስምምነት ነው፡፡ ስምምነቱ ሀገራት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች በጦርነት ውስጥ በቀጥታ ተካፋይ እንዳይሆኑ የተቻላቸውን እርምጃ ሊወስዱ እና ለጦር ኃይላቸው ከመመልመል ሊታቀቡ እንደሚገባ ይደነግጋል። ዕድሜያቸው በ15 እና በ18 ዓመት መካከል ያሉትንም ሲመለምሉ በዕድሜያቸው ከፍ ላሉት ቅድሚያ መስጠት እንዲሁም በጦርነት ወይም ግጭት ወቅት ሀገራት በራሳቸው ላይ ተፈጻሚነትና ለሕፃናት አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕጎች እና ደንቦች ማክበርና መከበራቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1949 ሲቪል ሰዎችን በጦርነት ጊዜ ለመጠበቅ የወጣው የጄኔቫ ስምምነት ሕፃናት በጦርነት ወቅት ጥበቃ ከሚደረግላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል መሆናቸውን እና ማንኛውም አካል በወታደርነትና በሌሎች የውትድርና አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሌለበት ይደነግጋል፡፡ የጄኔቫ ስምምነቶችን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የትጥቅ ግጭቶች ጉዳተኞችን ለመጠበቅ የወጣው የጄኔቫ ስምምነቶች ተጨማሪ ፕሮቶኮል1 ቁጥር 1 ሕፃናት በተለይም በወታደርነት እንዳይመለመሉ ተፋላሚ ኃይሎች የሚችሉትን ማናቸውንም እርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ያልሆኑ የትጥቅ ግጭቶች ጉዳተኞችን ለመጠበቅ የወጣው የጄኔቫ ስምምነቶች ተጨማሪ ፕሮቶኮል2 ቁጥር 2 በተመሳሳይ ሁኔታ ሕፃናትን ለውትድርና መመልመልን ይከለክላል፡፡
ሕፃናትን በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ መሳተፍን አስመልክቶ የወጣው የሕፃናት መብቶች ስምምነት አማራጭ ፕሮቶኮል (Optional Protocol to the Convention on the Rights of the Child on the Involvement of Children in Armed Conflict) በጦርነት ወይም በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሕፃናት ተሳትፎን በተመለከተ ተፈጻሚ የሚሆን የዓለም አቀፉ የሕፃናት መብቶች ስምምነት የመጀመሪያው ፕሮቶኮል ሲሆን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2014 አጽድቃዋለች፡፡ ፕሮቶኮሉ አባል ሀገራት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆናቸውን የሠራዊት አባላት በጦርነት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ሁሉንም ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ፣ የፈቃደኝነት ምልመላን በተመለከተ በሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 38 (3) የተቀመጠውን ዝቅተኛውን የ15 ዓመት ዕድሜ ከፍ እንዲል እና ከ18 ዓመት በታች ለሆኑት አባላት ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም አማራጭ ፕሮቶኮሉ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በማናቸውም ሁኔታ አስገድዶ ወይም ያለፈቃድ በሠራዊት አባልነት መመልመል እንደማይቻል እና ከመንግሥት ውጪ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችም በማናቸውም ሁኔታ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎችን የታጣቂ ቡድኑ አባል አድርገው መመልመል እንደማይችሉ ደንግጓል።
በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ማንኛውንም አስከፊ የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት እና አፋጣኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ የወጣ የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ስምምነት (ILO Convention No. 182 on the Prohibition and Immediate Action for the Elimination of the Worst Forms of Child Labor) ሕፃናትን በማስገደድ ለውትድርና መመልመል አስከፊ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እንደሆነ እና መንግሥታት ይህን መከላከል እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡
አህጉራዊ የሕግ ማዕቀፍ
የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር ሕፃናት በጦርነት ወይም በግጭት ውስጥ እንዳይሳተፉ በተለይም በጦር ሠራዊት አባልነት እንዳይመለመሉ ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወስዱ ቻርተሩን በፈረሙት ሀገራት ላይ ግዴታ ይጥላል፡፡ ቻርተሩ ሕፃን ማለት ማንኛውም ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ነው በማለት ትርጉም የሚሰጥ በመሆኑ በማናቸውም ሁኔታ በማንኛውም አካል ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በቀጥታ በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ እንዳይሆኑ እና ሕፃናትን ለውትድርና መመልመልን ይከለክላል፡፡ ከዚህ አንጻር ቻርተሩ ከሕፃናት መብቶች ስምምነት እና ከአማራጭ ፕሮቶኮሉ የተሻለ ለሕፃናት ጥበቃ ያደርጋል፡፡
የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት የባለሞያዎች ኮሚቴ በግጭት ውስጥ ያሉ ሕፃናትን አስመልክቶ በሰጠው አጠቃላይ ትንታኔ በግጭት ውስጥ ያሉ ሕፃናትን ጨምሮ ሕፃናት ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ጉዳዮች ሁሉ ሀገራት የሕፃናት ደኅንነትን(ጥቅምን) ቅድሚያ የመስጠት መርሕ ሊከተሉ እንደሚገባ ያስገነዝባል። በትጥቅ ግጭት ወይም ተጽዕኖ ውስጥ ያሉ ሕፃናት መብቶችን የማስጠበቅ ግዴታ ሕግ የማውጣት፣ አስተዳደራዊ እና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድን ያጠቃልላል።
በኢትዮጵያ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች ምን ይመስላሉ?
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሕፃናት ወታደሮችን የሚመለከት ግልጽ አንቀጽ አላካተተም፡፡ ይሁን እንጂ በአንቀጽ 36 ሥር ሕፃናት በሕይወት የመኖር፣ መንግሥት ሕፃናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሕፃናት ደኀንነት በቀደምትነት ከግምት በማስገባት መወሰን እና እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት፣ ከጉልበት ብዝበዛ የመጠበቅ፣ በትምህርት፣ በጤናቸው እና በደኀንነታቸው ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ሥራዎች የመጠበቅ መብት እንዳላቸው የሚያስቀምጥ በመሆኑ፤ ሕፃናትን በወታደርነት መመልመል ወይም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ በሰብአዊ መብቶቻቸው ላይ ጉዳት እና ጥሰት ስለሚያስከትል በሕገ መንግሥቱ የተከለከለ ድርጊት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ማንም ሰው በጦርነት፣ በግጭት ወይም በጠላት ወረራ ጊዜ የዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎችን እና የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግጋትን በመጣስ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ በማደራጀት፣ በማዘዝ ወይም ድርጊቱን በመፈጸም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆችን በጦርነት ውስጥ እንዲሳተፉ ለማድረግ ለወታደራዊ አባልነት መመልመል በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈጸም የወንጀል ድርጊት እንደሆነ እና ከ5 ዓመት እስከ 25 ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም ነገሩ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል እና ሕፃናትን በጦርነት ወይም በግጭት ውስጥ ማሳተፍ የጦር ወንጀል እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
የተሻሻለው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁ.1100/2011 እና የመከላከያ ሠራዊት አስተዳደር የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁ. 460/2012 ከሕፃናት የሠራዊት ምልመላ ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያላቸው ሕጎች ናቸው፡፡ አዋጁ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አባልነት የሚመለመሉ ሰዎችን ዝቅተኛ ዕድሜ በተመለከተ ግልጽ ድንጋጌ አላስቀመጠም፡፡ ሆኖም ማንኛውም ለውትድርና አገልግሎት ፈቃደኛ እና ብቁ የሆነ ኢትዮጵያዊ ለመከላከያ ሠራዊት አባልነት መከላከያ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመዘኛ መሠረት ሊመለመል እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው ደንብ ቁ. 460/2012 መከላከያ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመዘኛ መሠረት ማንኛውም ዕድሜው ከ18 እስከ 22 የሆነ ኢትዮጵያዊ በመከላከያ ሠራዊት አባልነት ሊመለመል እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም ተመልማዩ 18 ዓመት የሞላው ስለመሆኑ መከላከያ ሚኒስቴር በምን ዐይነት መንገድ እና ማስረጃ ማረጋገጥ እንዳለበት እንዲሁም የምልመላ ዝርዝር ሂደትን አላስቀመጠም፡፡
ሕፃናት ለውትድርና እንዳይመለመሉ እና መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ ይገባል?
- ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ለውትድርና አገልግሎት እንዳይመለመሉ የሀገር ውስጥ ሕጎች የሕፃናት ደኅንነትን/ጥቅምን ከማስቀደም መርሕ አንጻር የተቃኙ መሆን አለባቸው።
- መንግሥታትም ሆኑ በሕፃናት ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ሕፃናትን ለውትድርና መመልመልና ማሰማራት ያለውን ጉዳት እና ሊያደርስ የሚችለውን የመብት ጥሰት ለማኅበረሰቡ፣ ለሕግ አስፈጻሚ አካላት እንዲሁም ለሕፃናት ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ይኖርባቸዋል።
- የሕፃናት የልደት ምዝገባ አገልግሎትን በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ እንዲሆን እና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚመለከቱትን ሕጎች በአግባቡ ማስፈጸም ያስፈልጋል።
- የታጠቁ ቡድኖች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕጎችን በማክበር በማናቸውም ደረጃ ሕፃናትን በታጣቂነት ከመመልመል መቆጠብ እና በታጣቂነት የተሳተፉ ሕፃናት ካሉም በአስቸኳይ በቂ ማገገሚያ እንዲያገኙ በመተባበር ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ማድረግ ይጠበቃል።