የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን /ኢሰመኮ/ ምግብ በማግኘት መብት እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብ (human rights-based approach) ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡ ስልጠናው ታኅሣሥ 18 እና 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠ ሲሆን ከክልሎች የተውጣጡ የሸማቾች ማኅበራት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ስልጠናው ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ሩራል ኮንስትራክሽን (International Institute for Rural Reconstruction) ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ኢሰመኮ በቂ ምግብ የማግኘት መብትን እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብን በተመለከተ ገለጻ አድርጓል። በተጨማሪም ምግብ የማግኘት መብትን በተመለከተ በመጠን እና በጥራት በቂ፣ የተመጣጠነ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ በተጠቃሚው ባህል ተቀባይነት ያለው ምግብ ማግኘት እና ዘለቄታዊ ተደራሽነትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በስልጠናው የሰብአዊ መብቶች ምንነት፣ በቂ ምግብ የማግኘት መብት፣ የሰብአዊ መብቶች እና የምግብ ሥርዓት ግንኙነት እና ተያያዥ የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም በምግብ ሥርዓት ውስጥ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብ የመከተል አስፈላጊነት ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም በምግብ ሥርዓት ውስጥ መብትን መሠረት ያደረገ አቀራረብ ዋና ዋና መርሖች፣ አስፈላጊነት እና በመርኃ ግብሮችና ፕሮጀክቶች ውስጥ ማካተት የሚቻልበት ሂደት ተብራርቷል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች ከማሳ እስከ ገበታ ባለው የምግብ ሥርዓት ውስጥ ያሉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትን፣ በሥርዓቱ ውስጥ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዲሁም ሊጣሱ የሚችሉ መብቶችን ለይተዋል። እንዲሁም በሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ የመብት ጥሰቶችን መቅረፍ የሚቻልበትን መንገድ እና በቂ ምግብ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ የእያንዳንዱን ባለድርሻ አካል ሚና በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል። በእነዚህም ዙርያ ያሉ ተግዳሮቶች እና መልካም አጋጣሚዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
የኢሰመኮ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል፣ በቂ ምግብ የማግኘት መብት ከሰብአዊ መብቶች አንዱ መሆኑን ገልጸው በምግብ ሥርዓቱ ውስጥ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እና ሊጣሱ የሚችሉ መብቶችን መለየት ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።