በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ የተጀመረው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ ከኅዳር 28 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ፣ በአዲስ አበባ እና በሃዋሳ ከተሞች መካሄዱ ይታወሳል። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ከተሞች የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ጀምሯል።
ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነት እና ፍትሕ ለሁሉም በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ሰፊ ተደራሽነት ያለውን የፊልም ጥበብን በመጠቀም እና ስለ ሰብአዊ መብቶች ያለውን ግንዛቤ ለማዳበር በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች በፌስቲቫሉ ለእይታ እና ለውይይት ይቀርባሉ። በፌስቲቫሉ ሰብአዊ መብቶችን ማዕከል ያደረጉ አዳዲስ እና ከዚህ በፊት ለዕይታ የቀረቡ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ተቀባይነትን ያተረፉ የሙሉ ጊዜ እና አጫጭር ፊልሞች እንዲሁም ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
በአምስቱ ከተሞች የሚካሄደው ሁለተኛው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል፡-
- በአዳማ- ታኅሣሥ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በኦሊያድ ሲኒማ፣
- በአዲስ አበባ- ታኅሣሥ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ
- በባሕር ዳር- ታኅሣሥ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል፣
- በሃዋሳ- ታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሌዊ ሲኒማ እንዲሁም፣
- በጅግጅጋ- ታኅሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በኤምሲኤም ሆቴል የሚካሄድ ይሆናል፡፡
15 ፊልሞች ለእይታ የተሰናዱበትና በመዓዛ ወርቁ ፊልም ፕሮዳክሽንስ አስተባባሪነት የሚዘጋጀው ይህ ፌስቲቫል በሴቶችና ሕፃናት መብቶች፣ በስደተኞች፣ ፍልሰተኞች እና በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች፤ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች፣ በፍትሐዊ እና ሰብአዊ የሥራ ክፍፍል፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እና ጥቃት፣ እንዲሁም በማረሚያ ቤት የወጣት ጥፋተኞች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች ተካተውበታል፡፡ ፊልሞቹ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ እና ሲዳምኛ ቋንቋዎች የተሠሩ ወይም አጋዥ ጽሑፍ (subtitle) አካተዋል፡፡
ፌስቲቫሉን በይፋ ለማስጀመር በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ በሀገራችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አሁን ላለበት አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ለመድረሱ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ስለ ሰብአዊ መብቶች ያለው አነስተኛ ግንዛቤ በአሉታዊ መልኩ አስተዋዖ አድርጓል ብለዋል። አክለውም ኢሰመኮ በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱ ከለያቸው ቁልፍ የውጤት መስኮች መካከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እንዲኖር ማስቻል ሲሆን የኪነጥበብ ዘርፉ የሰብአዊ መብቶችን ግንዛቤ ከማስፋፋት እና ከማስተማር አኳያ ከፍያለ ሚና ይጫወታል። ይህ የሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ የፊልም ፌስቲቫል በሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት፣ ለመመማማር እና በሰብአዊ መብቶ መርሆች የታነጸ ትውልድን ለመቅረጽ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው ኢሰመኮ “ሰብአዊ መብቶች ባሕል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለውን ራዕይ ለማሳካት የትምህርትና የስልጠና ተቋማት፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ዘርፉ የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤን ለማዳበር፣ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎችን ለማስተዋወቅ እና ለማኅበረሰቡ ለማሰራጨት አስተዋጽዖ ያላቸው በመሆናቸው ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል።
በፌስቲቫሉ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው በፊልም እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ በሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኀን፣ ተማሪዎች እና ሌሎች ተመልካቾች ይታደሙበታል፡፡