የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሉተራን የዓለም ፌዴሬሽን (LWF) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ለሚገኙ በስደተኞች የሚመሩ ድርጅቶች እና ለስደተኞች ተወካዮች የሁለት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰኔ 19 እና 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰጥቷል። በስልጠናው በስደተኞች የሚመሩ ድርጅቶች ኃላፊዎች እና አባላት እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ በአዲስ አበባ የሚገኙ የከተማ ስደተኛ ማኅበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የስልጠናው ዋና ዓላማ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ መርሖችን እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን ጨምሮ ስለ መሠረታዊ የስደተኞች መብቶችና ግዴታዎች ተሳታፊዎች ያላቸውን ዕውቀት እና ግንዛቤ ማሳደግ ነው።

በግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በስደተኞች የሚመሩ ማኅበራት ሚናዎች እና ኃላፊነቶች፣ በስደተኞች መብቶች እና ጥበቃ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች አሳታፊነት እና አካታችነት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት እና አገልግሎት ሰጪዎች ጋር የሚከወን ቅንጅታዊ አሠራር ላይ ያተኮሩ ማብራሪያዎች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጋር በተግባር የተደገፈ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ የስደተኞች ሕግጋት እና ፖሊሲዎች፣ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ በስደተኞች የሚመሩ ማኅበራትን ማደራጀት እና ለመብቶቻቸው መከበር እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔዎችን ማምጣት የሚችሉበት አሠራር፣ የፕሮግራም ዕቅድ አዘገጃጀት፣ በፖሊሲ ውይይት ላይ የስደተኞች ተሳትፎ አስፈላጊነት እንዲሁም በስደተኞች፣ በመንግሥት ተቋማት እና በሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች መካከል ትብብርን ማሻሻል የሚሉት በስልጠናው የተዳሰሱ ጉዳዮች ናቸው።

የስልጠናው ተሳታፊዎች የሕይወት ልምዳቸውን እና ድርጅታዊ አሠራራቸውን ያጋሩ ሲሆን ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተግባራዊ በማድረግ ተቋማዊ ዐቅማቸውን ለማጠናከር እና ማኅበረሰባቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች ሰብአዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ “በስደተኞች መብቶች እና ግዴታዎች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር በስደተኞች የሚመሩ ማኅበራትን የውትወታ እና የአመራር ዐቅም ለማጎልበት እንዲሁም የስደተኛ ማኅበረሰቦች ድምጽ ትርጉም ባለው መልኩ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ዓይነተኛ ሚና አለው” ብለዋል። አክለውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች መብቶች ጥበቃን ለማጎልበትና አሳታፊ የሆኑ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች እና አሠራሮች እንዲተገበሩ የስደተኛ ማኅበረሰብ ተወካዮችን እና በስደተኞች የሚመሩ ማኅበራትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።