የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ ያደረገውን 2ኛው የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ለማስተዋወቅ እና ውትወታ ለማድረግ ከባለመብቶች እና ከባለግዴታዎች ጋር ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ የፌዴራል እና የክልል ከተሞች የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን ማኅበራት፣ የመንግሥት ተቋማት እና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ያካተታቸውና በ2016 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የታዩ ቁልፍ እመርታዎች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። እንዲሁም በአረጋውያን እና በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ ሁለት የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በተጨማሪም በሪፖርቱ ውስጥ አረጋውያንን የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ እንደ አሳሳቢ ሁኔታ ተጠቅሶ የነበረ ቢሆንም ዓመታዊ ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ኢትዮጵያ ፈርማ የሕጎቿ አካል እንዲሆን የተስማማችው የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርታር የአፍሪካ አረጋውያን ፕሮቶኮል ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ሁኔታዎችን ለማሻሻል የሚኖረው አስተዋጽዖ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች ላይ ባተኮረው የመጀመሪያው የፓናል ውይይት ኢሰመኮ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አረጋውያን እና ጡረተኞች ማኅበር እና ኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል (HelpAge International) ተሳትፈዋል። በውይይቱ በግጭት ዐውድ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ነባራዊ ሁኔታ፣ ከጤና መድኅን አገልግሎት ጋር በተገናኘ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በተለይም በመንግሥት የጤና ተቋማት የመድኅን ሽፋን ላላቸው አረጋውያን ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተገናኘ መድኃኒቶች እያሉ የለም የሚባልበት ሁኔታ መኖሩ፣ በኮሪዶር ልማት ምክንያት ቤቶቻቸው ለሚፈርሱ አረጋውያን ተደራሽ የሆኑ ምትክ ቤቶችን ከመስጠት አኳያ ክፍተቶች መስተዋላቸው፣ የጡረታ አበል ተከፋይ የሆኑ አረጋውያን እንዲሁም ከጡረታ ሥርዓት ውጪ የሆኑ እና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያን በቂ ምግብ ለማግኘት መቸገራቸው በተሳታፊዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ናቸው።
በተጨማሪም በአረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ እና ንብረትን መሠረት ያደረጉ የቤት ውስጥ ጥቃቶች መበራከታቸው፣ አረጋውያን መብቶቻቸውን ለማስከበር በሚል የመሠረቷቸው ማኅበራት ጽሕፈት ቤቶች በኮሪዶር ልማቱ ምክንያት እንዲፈርሱ ሲደረግ አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ተሟልቶ ባለመከናወኑ የማኅበራት ንብረት መዘረፉ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ስለአረጋውያን መብቶች ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ አረጋውያን ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑ በውይይቱ ከተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ናቸው።
የአካል ጉዳተኞች መብቶች ላይ ባተኮረው በሁለተኛው የፓናል ውይይት ኢሰመኮን ጨምሮ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ተሳትፈዋል። በውይይቱም የሕግ ማሻሻያዎች እና የኮሪዶር ልማት አካል ጉዳተኞች ላይ የሚፈጥሯቸው አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖዎች፣ በትምህርት ዘርፍ ከአእምሮ እድገት ጋር የተገናኘ ጉዳት ያሉባቸውን ተማሪዎች የማካተት ክፍተት እና አነስተኛ ግንዛቤ መኖሩ እንዲሁም ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች እምብዛም ውጤታማ አለመሆናቸው በተሳታፊዎች ተጠቁሟል። በሌላ በኩል በተጓተተ የመጽደቅ ሂደት ላይ የሚገኘው የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ሕግ ጸድቆ በአፋጣኝ ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በጋራ የመሥራት አስፈላጊነት አጽንዖት ሊሰጠው እንደሚገባ የተጠቀሰ ሲሆን በዚህ ረገድ ኢሰመኮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመራቸውን የውትወታ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተመላክቷል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ አረጋውያን መብቶችቻቸውን እንዲያውቁ እና እንዲጠይቁ ለማድረግ እና ማኅበራቶቻቸውን ለማጠናከር ሰፊ ሥራ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢሰመኮ በዚሁ ውይይቱ በተካሄደበት ሳምንት የጀመረውን የአረጋውያን ስልጠና አስፋፍቶ በመቀጠል የበኩሉን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ገልጸዋል። አክለውም የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች የመብት ጥያቄ ምላሽ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ በውይይቱ ላይ የተሳተፉትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።