የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሕግና ፖሊሲ ቀረጻ እንዲሁም ትግበራ ሂደቶች የሚሳተፉ አካላት የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች በተሟላ መልኩ እንዲያካትቱ ለማስቻል የተዘጋጀ የማረጋገጫ መዘርዝር (guiding checklist) ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ከልዩ ልዩ የመንግሥት ተቋማት፣ ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
ውይይቱ በልዩ ልዩ ዘርፎች ሕጎችና ፖሊሲዎች ሲቀረጹ እና ሲፈጸሙ የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች በተሟላ መልኩ እንዲያካትቱ ለማስቻል ኢሰመኮ ያዘጋጀውን የማረጋገጫ መዘርዝር በሂደቱ ለሚሳተፉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ ባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ ያለመ ነው፡፡
የአካል ጉዳተኞች የትምህርት፣ የጤና፣ የሥራና ቅጥር፣ የሕግ ችሎታ፣ ፍትሕ የማግኘት፤ ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት እንዲሁም በፖለቲካዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ተሳትፎ የማድረግ መብቶችን ምንነት፤ በእነዚህ መብቶች ዙሪያ ያሉ ብሔራዊ የሕግና ፖሊሲ ማእቀፎች ክፍተቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች በውይይቱ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም ሕግና ፖሊሲ የማውጣት እንዲሁም የመተግበር ሥልጣን እና ኅላፊነት ያላባቸው አካላት በሕግና ፖሊሲ ቀረጻ እንዲሁም ትግበራ ሂደቶች የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች መካተታቸውን ወይም አለመካተታቸውን በቀላሉ መለየት የሚያስችሏቸው የማረጋገጫ ነጥቦች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በውይይቱ መክፈቻ ባስተላለፉት መልእክት፤ አካል ጉዳተኝነትን አስመልክቶ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታዩ የተዛነፉ ዕይታዎች በሀገር አቀፍ ሕጎችና ፖሊሲዎች ውስጥ ሲንጸባረቁ እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው “በሕግና ፖሊሲ ቀረጻ እንዲሁም ትግበራ ሂደቶች ውጤታማ እና ትርጉም ያለው የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ ይገባል” ብለዋል፡፡ አክለውም “ውጤታማ እና ትርጉም ያለው የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎን ለማረጋገጥ የግምገማና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ቁልፍ ተግባራት ናቸው” ሲሉ አብራርተዋል።