የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2016 ዓ.ም. የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎትን የሚያዳብሩ ስድስት ስልጠናዎች ለወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ማኅበራት አባላት፣ ለማረሚያ ቤት ፖሊሶች፣ ለፖሊስ አባላት እና አመራሮች፣ ለሲቪክ ማኀበራት እና ለመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች ሰጥቷል፡፡ ስልጠናዎቹ በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች፤ በሴቶች መብቶች፤ በተጠርጣሪዎች መብቶች፣ በሕግ በታራሚዎች መብቶች እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
ለወጣቶች፡- የሰብአዊ መብቶች ከሰላም፣ መቻቻል እና አብሮ መኖር አንጻር
ኢሰመኮ ከሰብአዊ መብቶች፤ ሰላም፣ አብሮነት እና መቻቻል አኳያ የወጣቶች ሚናን ለማሳደግ ያለመ ስልጠና በአማራ፣ በሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና የወጣት አደረጃጀቶች ለተውጣጡ 38 አባላት በሃዋሳ ከተማ ከሐምሌ 10 እስከ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ስልጠናው ወጣቶች ስለሰብአዊ መብቶች እና ስለሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ሰላም፣ መቻቻል እና አብሮ መኖር ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚና እና ኃላፊነቶች ዕውቀታቸው እና አመለካከታቸው እንዲገነባ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ለወጣቶች፡- ሰብአዊ መብቶች እና የሽግግር ፍትሕ
ኢሰመኮ በሽግግር ፍትሕ ፅንሰ-ሐሳብ እና ሂደቶች ዙርያ እንዲሁም ከሰብአዊ መብቶች ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ወጣቶች በቂ ዕውቀት እንዲያገኙ እና በሂደቱ ለመሳተፍ ተነሳሽነት እንዲያዳብሩ ከሲዳማ ክልል እና ከሃዋሳ ከተማ ለተውጣጡ 34 የወጣት ማኅበራት አባላት እና አመራሮች የአሰልጣኞች ስልጠና በሃዋሳ ከተማ ከመስከረም 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰጥቷል፡፡ ስልጠናው የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች የቀረቡበት ሲሆን የወጣቶችን ጉልህ ሚና ለማሳደግ ተግባራዊ ልምምዶች እንዲያደርጉ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ስልጠናው ወጣቶቹ በስልጠና ያገኙትን ዕውቀት እና ተሞክሮ ለማኅበር አባላቶቻቸው ማካፈል የሚችሉበትን ዐቅም ለመገንባት ያለመ ነው፡፡
የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስልጠና
ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶችን አስመልክቶ ከሃዋሳ ከተማና ከዙሪዋ እንዲሁም ከሻሸመኔ ከተማ ለተውጣጡ 34 የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት አመራሮችና አባላት ከመስከረም 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው የሰብአዊ መብቶች እሴቶች እና መርሖች እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን የተመለከቱ ሰነዶች በሰፊው ማብራሪያ ቀርቦባቸዋል፤ የቡድን ውይይትም ተደርጎባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የስልጠናው ተሳታፊዎች ለማኀበራቸው አባላት እና ተጠቃሚዎች የሚሰጡት አገልግሎት መብትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የሚያግዝ ዕውቀት እና አመለካከትን የሚገነባ ይዘቶች እና ተግባራዊ መልመጃዎች ተካተዋል፡፡
ለመብት ባለግዴታዎች፦ የሴቶች መብቶች ስልጠና
ኢሰመኮ የሴቶችን መብቶች በተመለከተ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለግዴታ ተቋማት ያለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ የሚያግዝ ስልጠና ከመስከረም 21 እሰከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ቀናት በድሬዳዋ ከተማ ሰጥቷል፡፡ ተሳታፊዎቹ በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አስፈጻሚ የመንግሥት አካላት እና በሴቶች መብቶች ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ 39 ባለሞያዎች እና አመራሮች ናቸው፡፡ ስልጠናው ስለሴቶች መብቶች ዕውቀት ማስጨበጥ፣ አመለካከትን ማጎልበት እንዲሁም ተሳታፊዎች ያገኙትን ዕውቀትና አመለካከት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡ በስልጠናው በኢሰመኮ ክትትል የተለዩ የሴቶች መብቶች ጉዳዮች እና ከሥርዓተ ጾታ እኩልነት ጋር በተገናኘ በሁሉን አቀፍ አቻ ግምገማ ለኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በተመለከተ ጠለቅ ያለ ገለጻ እና ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም ተሳታፊዎች በአከባቢያቸው የሚስተዋሉ የሴቶች መብቶች ጥሰቶችን በመለየት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች በቡድን ውይይት ሐሳብ እና ልምድ እንዲለዋወጡ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡
ለማረሚያ ቤት ፖሊሶች እና አመራሮች፦ የሕግ ታራሚዎች መብቶች ስልጠና
ኮሚሽኑ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶችን ከማክበር፣ ማስከበር እና ማሟላት አኳያ ያለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና በድሬዳዋ ከተማ ከመስከረም 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ሰጥቷል፡፡ የስልጠና ተሳታፊዎቹ በሐረሪ እና በሶማሊ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስታዳደር ሥር ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ 35 የማረሚያ ቤት ፖሊሶች እና አመራሮች ሲሆኑ በስልጠናው ላይ በታራሚዎች አያያዝ የተሻለ አፈጻጸም ካለው ጨንቻ ማረምያ ቤት ባለሞያዎችን በመጋበዝ ልምድ እና አሠራራቸውን እንዲያጋሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም የስልጠናው ተሳታፊዎች ባሉ ነባራዊ ሁኔታዎችም ቢሆን ለታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በተሻለ መልኩ መሥራት እንደሚቻል የተረዱ ሲሆን ለሰብአዊ መብቶች መከበር እንዲሠሩ ተነሳሽነት አሳድረዋል፡፡
ለፖሊስ አባላት እና አመራሮች፦ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና
ኢሰመኮ ፖሊሶች ከሥራቸው ጋር ተዛማጅ ስለሆኑ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች ምንነት እና ተግባራዊነት እንዲሁም የፖሊስ ተጠያቂነትን በተመለከተ ዕውቀታቸው፣ አመለካከታቸው እና ክህሎታቸውን ለመገንባት ያለመ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ከሐረሪ እና ከሶማሊ ክልሎች የተውጣጡ 34 የፖሊስ አባላትና አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው ከመስከረም 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ተሳታፊዎቹ ፖሊስ የሰዎችን መብቶችና ነጻነት በመጠበቅ፣ የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር እንዲሁም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የሰው ልጆች ያለሥጋት በሰላም እንዲኖሩ ከፍተኛ እና የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመረዳት ተጠርጣሪዎችን በሚይዙበትና በቁጥጥር ሥር በሚያውሉበት፣ የወንጀል ምርመራ በሚያደርጉበት እንዲሁም የኃይልና የጦር መሣሪያ በሚጠቀሙባቸው ጊዜያት ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው ተሳታፊዎች መልካም ተሞክሮዎቻቸውን ለውይይት እንዲያቀርቡ እና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ዕድል ፈጥሯል፡፡