የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት ረገድ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር ያለመ የባለሙያዎች ውይይት ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል።

ኢሰመኮ ሚያዝያ 15 እና 16 ቀን 2017 ዓ.ም. የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን አስመልክቶ ባካሄደው ብሔራዊ ኮንፈረንስ ማጠቃለያ ላይ በዘርፉ ከሚሠሩ የፌዴራል እና የክልል መንግሥት ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤቶች፣ የአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተውጣጥቶ የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሜቴ አባላት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ እና የዴንማርክ ሰብአዊ መብቶች ተቋም ተወካዮች በውይይቱ ላይ በአማካሪነት ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ፍትሕ ሚኒስቴር በተለያዩ የውይይት መድረኮች በተሰጡ አስተያየቶችና ግብአቶች መሠረት ያሻሻላቸው የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ ይዘቶች ለኮሚቴው ቀርበው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ውይይት ተደርጎባቸዋል። በተጨማሪም በ2018 በጀት ዓመት ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከማስፋፋት አንጻር ተግዳሮቶችንና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በቅንጅት መሠራት የሚገባቸው ተግባራትን በመለየት የድርጊት መርኃ ግብር ተዘጋጅቷል። ኢሰመኮ እና የፍትሕ ሚኒስቴር የድርጊት መርኃ ግብሩን የማጠናቀቅ እንዲሁም የማጽደቅ እና የማስፈጸም ሂደቱን የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ (በቀኝ)

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ በቅንጅት እና በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። አክለውም ኢሰመኮ አገልግሎቱ የሚመራበት ሕግ እና ሥርዓት እንዲዘረጋ እና የማኅበረሰቡን ፍትሕ የማግኘት መሠረታዊ መብት እውን ለማድረግ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የመሥራት እና የማስተባበር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።