የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በየዓመቱ የሚታሰበውን “በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃት ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን” በማስመልከት ከአረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር እና ሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል (HelpAge International) ጋር በመተባበር መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ ተቋማት እና የአረጋውያን ማኅበራት ተወካዮች የተሳተፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል።

ውይይቱ የዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ መሪ ቃል በሆነው “በመንከባከቢያ ማዕከላት የሚገኙ አረጋውያን ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች በመረጃ እና እርምጃ ምላሽ መስጠት” (“Addressing Abuse of Older Adults in Long Term Care Facilities: Through Data and Action”) እንዲሁም የኢትዮጵያ አረጋውያን እና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር “በየትኛውም ቦታ እና ሁኔታ የአረጋውያን ጥቃትን በጋራ እንግታ!” በሚለው መሪ ቃል ላይ በመመርኮዝ አረጋውያን ላይ የሚደርሱ የጥቃት ዐይነቶችን የሚያሳዩ እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን የሚያስረዱ ገለጻዎች ቀርበው የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የአረጋውያን ማኅበራት ተወካዮች አረጋውያን ለዘርፈ ብዙ የመብት ጥሰቶች ተጋላጭ እንደሚሆኑ እና በተለይም የኢኮኖሚ ጥገኛ መሆናቸው የጥቃት ተጋላጭታቸውን በእጅጉ እንደሚያሰፋው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ቦርድ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ አረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አሳሳቢ መሆናቸውን እና በማኅበረሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ ተጠቂዎች ፍትሕ እያገኙ አለመሆኑን ገልጸዋል። አክለውም አረጋውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን፤ በተለይ ደግሞ መንግሥት ዋነኛው ባለግዴታ እንደመሆኑ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል ቀዳሚውን ድርሻ ሊወስድ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕጻናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በበኩላቸው በተለያዩ መንከባከቢያ ማእከላት የሚገኙ አረጋውያን ለዘርፈ ብዙ የመብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል። አያይዘውም የበጎ አድራጎት መርሕ ላይ የተመሠረቱ የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት የአረጋውያኑን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን እና መከበርን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና አገልግሎቶቻቸው የሰብአዊ መብቶች መርሕን የተከተለ እንዲሆን አሳስበዋል።