የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መብቶቻቸው የተጣሱባቸው አቤቱታ አቅራቢዎች የተለያዩ የሕግ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ ማግኘት የሚችሉበትን እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የቅብብሎሽ ሥርዓት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመዘርጋት በዘርፉ ከተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ የጋራ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ተወካይ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፣ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር፣ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ኃላፊ፣ የእንባ ጠባቂ ተወካዮችን ጨምሮ 36 የሚሆኑ በፍትሕ ዘርፉ የተሰማሩ መንግሥታዊ ተቋማት፣ የሕግ፣ ማኅበራዊና ሥነልቦናዊ ድጋፍ የሚሰጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ አራት ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን በዋናነት በፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች የመኝታ እና አልባሳት እጥረቶች፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አለመኖር፣ ለሴት ታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ ግብዓቶች አለመኖር፣ የማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፎች አለመኖር እንደ ክፍተት የተነሱ ነጥቦች ናቸው፡፡ በመቀጠልም የቅብብሎሽ ሥርዓት መዘርጋትን በተመለከተ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ሕጎች ላይ ሰፊ ትንታኔ ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም ኮሚሽኑ በምርመራ እና ክትትል ሥራ የገጠሙትን ክፍተቶች እንዴት በቅብብሎሽ ሥርዓት መፍታት እንደሚቻል እና የቅብብሎሽ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ እና ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
በተሳታፊዎች ከተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በክልሉ ነጻ የሕግ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን፣ የኢፌዴሪ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባለሙያ በሰጡት አስተያየት አስተዳደራዊ በደሎችን ይዘው የሚመጡ ባለጉዳዮችን ኮሚሽኑ ወደ ተቋሙ ቢልክ የተሻለ አገልግሎት እንደሚያቀርብ፣ ከሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ የመጡ ተሳታፊ በበኩላቸው ለሴት ተጠቂዎች የተሻለ ድጋፍ ለማድረግ ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን እና በቀጣይም ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር እንደሚሠሩ፣ በተለይም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሴቶች ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በበኩላቸው ለተጎጂዎች የተፋጠነ ድጋፍ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን በዚህም የሥነ ልቦና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ መሰጠቱን አንስተዋል፡፡ ማረሚያ ቤት የሚገኙ አፋጣኝ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ታራሚዎች ለመደገፍ በቋሚነት አምቡላንስ መመደብ የማይችሉ ቢሆንም ነገር ግን ጥያቄው ሲቀርብ ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች የመጡ ተወካዮችም በቀረበው የክትትል ግኝት መሰረት ያሉትን ክፍተቶች ለመለየት መቻላቸውን እንዲሁም በቀጣይ ማረሚያ ቤቶችን እና ፖሊስ ጣቢያዎችን ለመደገፍ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ በማጠቃለያ ንግግራቸው ኮሚሽኑ በምርመራ እና ክትትል ሥራዎች የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላትና ተጎጂዎች ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችላቸውን የቅብብሎሽ ሥርዓት ለመዘርጋት በክልሉ ያሉ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ያሳዩትን ድጋፍ እና እገዛ አድንቀው በቀጣይ የቅብብሎሽ ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡