መግቢያ 

  1. ይህ የሩብ ዓመት ሪፖርት በኢትዮጵያ የበጀት ዓመት አቆጣጠር መሠረት ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም. አጋማሽ ያለውን ጊዜ የሚመለከት ነው። ሆኖም የተወሰኑት ሁኔታዎች ቀደም ባሉት ወራት የተከሰቱና የቀጣይነት ባሕርይ ያላቸው በመሆናቸው ወይም የሰብአዊ መበቶች ክትትልና ምርመራ በቅርብ ጊዜ የተጠናቀቀ በመሆኑ በዚህ ሪፖርት እንዲካተቱ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ሥጋቶች እና አሳሳቢ ሁኔታዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህ የሩብ ዓመት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተለይ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ በዋነኝነት ከፍተኛ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢነታቸው በቀጠሉ ጉዳዮች ላይ ማሳያ በሆኑ ክስተቶች አጠቃላይ ምልከታ በመስጠት ለሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መሻሻል ምክረ ሐሳቦችን የሚያቀርብ ነው። 
  2. ሪፖርቱ በሩብ ዓመቱ ውስጥ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን  በሙሉ የሚሸፍን አይደለም። ይልቁንም በእነዚህ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የተሟላ ክትትልና ምርመራ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ውጤታማ ክትትልና ምርመራ የተከናወነባቸውን ጉዳዮች ብቻ በማሳያነት በመለየት ስለሰብአዊ መብቶች ሁኔታው አሳሳቢነት እንዲሁም በአፋጣኝ ሊወሰዱ የሚገባቸው የእርምት እርምጃዎችን የሚያመላክት ነው።  
  3. ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የሩብ ዓመት ሪፖርት የለያቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ጉዳዮች በዚህ የሪፖርት ጊዜም ቀጥለዋል። በዚህም በተለይ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ከፍርድ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል እና የዳኝነት ነጻነት መሸርሸር ይገኙበታል።  
    • ከፍርድ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ  
  4. ከፍርድ ውጪ የሚፈጸም ግድያ ቃሉ እንደሚያመለክተው ሆን ተብሎ ከፍርድ ቤት ሂደት እና ውሳኔ ውጪ በሰው ላይ የሚፈጸም ግድያ ሲሆን ከመብቶች ሁሉ መሠረታዊ ተደርጎ የሚወሰደውን በሕይወት የመኖር መብት የሚጥስ ነው። በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት እንዲሁም የንብረት መብቶች በሰላምም ሆነ በትጥቅ ግጭት ወቅት በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በተጨማሪ በትጥቅ ግጭት ወቅት ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕጎችም (international humanitarian laws) ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ በሲቪል ሰዎች እና በሲቪል ሰዎች መገልገያ ቁሶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ይከለክላል። በትጥቅ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች እነዚህኑ ዒላማ ከማድረግ የመቆጠብ፣ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተገቢውን ጥንቃቄ የማድረግ፣ ጥበቃ የተደረገላቸውን ሰዎችና ቁሶች ከወታደራዊ ዒላማዎችና ተዋጊዎች የመለየት (the principle of distinction) እና በኃይል እርምጃ ወቅት የተመጣጣኘነት መርሕን የማክበር ግዴታ አለባቸው።  
  5. በአማራ ክልል:- ከመስከረም 6 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ፣ ቀበሌ 18፣ አዲስ ዓለም፣ ገንፎ ቁጭ፣ ቆሸ ሰፈር፣ ፋሲል ካምፓስ፣ አማኑኤል፣ ሎዛ ማርያም፣ አጣጥ እና አዘዞ በተባሉ የከተማው አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል በነበረው የትጥቅ ግጭት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተጸፈመ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ጥቃት እንዲሁም በሁለቱም ወገን በነበረው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ሕፃናትን እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 10 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉና  በአካል እና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች እና የዐይን እማኞች ለማወቅ ተችሏል። ከአንድ ሆስፒታል  በተገኘ  መረጃ  ብቻ በግጭቱ ምክንያት 6 ሴቶች እና 6 ሕፃናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 32 ሲቪል ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 1 ሰው ሆስፒታሉ ውስጥ ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። 
  6. ከመስከረም 6 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል ከነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋር በተያያዘ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ዒላማን ባልለየ የጦር መሣሪያ ምክንያት ሕፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 4 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 3 ሕፃናትን ጨምሮ በ5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ድርሷል። በተጨማሪ ቢያንስ 6 የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል። 
  7. መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከዓለም በር ወደ ወረታ ሲጓዙ ወጅ የተባለ ቦታ ላይ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ጋር የተፈጠረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመንገድ ላይ አግኝተው እንዲሁም ከመኖሪያ ቤታቸው አስወጥተው የያዟቸውን በአጠቃላይ 10 ሲቪል ሰዎች ገድለው እንደሄዱ የዐይን እማኞች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል። ከተገደሉት መካከል አቶ አማረ ባይሌ የተባለ መምህር አንዱ ሲሆን፣ የመንግሥት የጸጥታ አባላት በአካባቢው አልፈው ሲሄዱ በመኖሪያ ቤቱ በር ላይ ሲያገኙት “እንፈልግሃለን” ብለው ወስደው እንደገደሉት ታውቋል። የሟች ቤተሰቦች ስለሁኔታው ሲያስረዱ “ከወሰዱት በኋላ በተደጋጋሚ የእጅ ስልኩ ላይ ስንደውል ቆይተን ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ላይ አንድ ሰው አነሳው። “አማረን ፈልገን ነበር” ስንለው “ጫካ ውስጥ ጥለነዋል እዚያው ፈልጉት” በማለት ስልኩን እንደዘጋባቸው ገልጸዋል። “ቁጭ ብለን አድረን ሲነጋ ስናፈላልግ ከአንድ ሌላ አስከሬን ጋር ተጥሎ አገኘነው” በማለት አስረድተዋል። ሌላው በዕለቱ ተገድሎ የተገኘው አቶ መንጋው አባቡ የተባለ የባጃጅ አሽከርካሪ ወጣት ሲሆን “ለፋኖ የትራንስፖርት አገልግሎት ትሰጥ ነበር” በሚል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንደገደሉት እና ባጃጁንም እንዳቃጠሉ የዐይን እማኞች ገልጸዋል። 
  8. መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ስናን ወረዳ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት አካባቢ አቶ ጌታ እንዳለ አንማው እና አቶ አትንኩት ሁነኛው የተባሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን ከመኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ የገደሏቸው ሲሆን በሌሎች 4 መምህራን ላይ ድብደባ ፈጽመዋል። በመምህራኑ ላይ የተፈጸመው ግድያ እና ድብደባ በ2017 ዓ.ም. ትምህርት ለማስጀመር ካደረጉት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የመረጃ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል። 
  9. ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ቢቡኝ ወረዳ፣ ወይንውሃ ቀበሌ በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድ “ፋኖን ትደግፋላችሁ” እና “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” ያሏቸውን 11 ሲቪል ሰዎች በመያዝ ወይንዉሃ ቀበሌ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ በመውሰድ እንደገደሏቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል። ከእነዚህም መካከል  አቶ ይርሳው አንተነህ፣ አቶ አዲስ ሞላ እና አቶ ብዙዬ አወቀ መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ የተገደሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከመስከረም መጨረሻ እስከ ጥቅምት አጋማሽ 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ተገድለው የተገኙ መሆኑን እንዲሁም የቀብር ሥነ-ሥርዓት እንዳይካሄድ ክልክላ የነበረ መሆኑን የመረጃ ምንጮች አስረድተዋል።  
  10. መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሊቦ ከምከም ወረዳ፣ አግድ ቀበሌ፣ ውሻ ጥርስ በተባለ ጎጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቤት ለቤት በመግባት “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” እንዲሁም “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል በ8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል። ከእነዚህም መካከል 1 የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር እናትን ጨምሮ 3 ሴቶች እና 1 ሕፃን ይገኙበታል። በተጨማሪም 2 ሲቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዳደረሱ እና ሌሎች 6 ሲቪል ሰዎችን ይዘው እንደወሰዱና ይህ ሪፖርት እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሰዎቹ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ የመረጃ ምንጮች አስረድተዋል።  
  11. መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ጉና በጌምድር ወረዳ፣ ክምር ድንጋይ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ አቶ ገደፋው አለሜ በተባሉ ሰው መኖሪያ ቤት ግቢ ላይ በማረፉ 2 የቤተሰቡ አባላት (ወ/ሮ ፍቅረዓለም አለበልና ሕፃን ዮርዳኖስ ገደፋው) ሲገደሉ ሌሎች 2 ሕፃናት ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ኢሰመኮ  ለማረጋገጥ ችሏል። ጥቃቱ ከተፈጸመበት 1 ቀን ቀደም ብሎ በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያ የተደረገ ቢሆንም በዕለቱ ግን (መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም.) ምንም ዐይነት ውጊያ ወይም ግጭት እንዳልነበረ ለመረዳት ተችሏል። 
  12. ከመስከረም 25 እስከ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ በደባይ ጥላትግን ወረዳ፣ በቁይ ከተማ እና በዙሪያ ቀበሌዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል በነበረ ውጊያ በሲቪል ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። በተለይ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት መጽሔት ልንገረው የተባለች የ3 ዓመት ሕፃን በተባራሪ ጥይት ተመትታ ቁይ ጤና ጣቢያ የሕክምና እርዳታ ከተደረገላት በኋላ ለከፍተኛ ሕክምና “ሪፈር” ብትባልም መንገድ በመዘጋቱ እና በወቅቱ ሕክምና ባለማግኘቷ ሕይወቷ ማለፉን ከቤተሰቦቿ ማረጋገጥ ተችሏል። መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በውጊያው የሞቱ ሰዎችን ሥርዓተ ቀብር ሲፈጽሙ የነበሩ 3 ሲቪል ሰዎች “ለምን ትቀብራላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲሆን፣ አንዱ መስማት የተሳነው አካል ጉዳተኛ መሆኑን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።  
  13. መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን፣ በቋራ ወረዳ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ይካሆ እና ገለጉ (አሶል) ቀበሌዎች በመግባት ነዋሪዎችን “የብልጽግናን መንግሥት ትደግፋላችሁ” እንዲሁም “ከመከላከያ ጋር ሆናችሁ ፋኖን ተዋግታችኋል” በሚል 8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል። በተጨማሪም 60 የሚሆኑ ሰዎችን ገለጉ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ለቀናት እንዳሰሩ እንዲሁም በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶችን እንደዘረፉ ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል። ጥቃቱን በመፍራት በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን ከቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ ለማወቅ ተችሏል። 
  14. መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ ዳጊ ቀበሌ ላይ በመንግሥት ኃይሎች በተደጋጋሚ በተፈጸመ የአየር ጥቃት አቶ ሞገስ ደፈርሻ የተባሉ የ70 ዓመት አረጋዊ እንደተገደሉና 2 ሴቶች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም ዳጊ ጤና ጣቢያ ላይ ጉዳት እንደደረሰ እና 4 መኖሪያ ቤቶች ተመተው እንደፈራረሱ ኢሰመኮ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በዕለቱ የአየር ጥቃት በተፈጸመባቸው ቦታዎችም ሆነ በቅርብ ርቀት ላይ ግጭት እንዳልነበረ እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት በቦታው እንዳልነበሩ ጨምረው ገልጸዋል። 
  15. መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል ከተደረገ የተኩስ ልውውጥ በኋላ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የደጋ ዳሞት ወረዳን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ወደ ወረዳው መቀመጫ ፈረስ ቤት ከተማ በመግባት በርካታ የወረዳ አመራሮችን፣ ሥራ ኃላፊዎችን እና “የመንግሥት የመረጃ ምንጭ ናቸው” ያሏቸውን ቢያንስ 80 ሰዎች አስረዋል። እንዲሁም የወረዳ አስተዳዳሪውን ጨምሮ 3 መኖሪያ ቤቶችን በእሳት እንዳቃጠሉ የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ከመስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት ሰዎች መካከል 38 ሰዎች ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 1፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ልዩ ቦታው ፈረስ ቤት ሚካኤል 1 ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) እንደተገደሉ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች አስረድተዋል። ሁሉም ሟቾች ሲቪል ሰዎች (የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች) ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 22ቱ ሰዎች ኢሰመኮ በስም የለያቸው ናቸው። 
  16. ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በደቡብ ሜጫ ወረዳ፣ ገርጨጭ (መሃል ገነት) ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን ግጭት ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ አባላት አቶ ገብሬ ሙሉዬ እና አቶ መሀሪው መኩሪያ የተባሉ 2 ሰዎችን “ከፋኖ ጋር በመሆን ስትዋጉን ቆይታችሁ ነው ወደ ቤታችሁ የገባችሁት” በማለት ከቤታቸው አውጥተው እንደገደሏቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። 
  17. ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 6፡20 አካባቢ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በደጋ ዳሞት ወረዳ፣ ፈረስ ቤት ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አማን እንየው የተባለ 1 የ4 ዓመት ሕፃን ልጅ ሲገደል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈረስ ቤት ቅርንጫፍ የሚገኝበት ሕንጻ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል። የድሮን ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ፈረስ ቤት በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደነበረ እንዲሁም በጥቃቱ በሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። 
  18. ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 3፡20 ሰዓት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ መንዝ ማማ ባሽ ንኡስ ወረዳ፣ “ጦስኝ አፋፍ” በተባለ አካባቢ በሚገኝ አንድ የመንገድ ተቋራጭ ድርጅት ሲጠቀምበት የነበረ ካምፕ ላይ በተፈጸመ የአየር (ድሮን) ጥቃት 2 ሕፃናትና 1 ሴት የተገደሉ ሲሆን በ5 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎችና የዐይን እማኞች ገልጸዋል። ተጎጂዎቹ ከ5 ዓመታት በፊት በመሬት መንሸራተት ምክንያት ባሽ ቀበሌ “ወራና ጨታ” ከተባለ ጎጥ ተፈናቅለው በዚሁ ካምፕ ተጠልለው ይኖሩ የነበሩ ናቸው። የድሮን ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት አካባቢው በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ሥር የሚገኝ እንደነበርና ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ታጣቂዎቹ የመጠጥ ውሃ ለመቅዳት፣ ለመታጠብ እና ምግብ ለማብሰል ወደ ካምፑ ይመጡ እንደነበር ጨምረው አስረድተዋል።  
  19. ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ ዞን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከወልድያ ከተማ ወደ ቃሊም ከተማ በተከታታይ የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ በሰው ሕይወትና አካል እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች እና የቤት እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ኢሰመኮ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያስረዳሉ። በወቅቱ ቃሊም ከተማ በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቁጥጥር ሥር ብትሆንም የጦር መሣሪያ በሚተኮስበት ወቅት በአካባቢው ምንም ዐይነት የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበረ ነዋሪዎች አስረድተዋል።  
  20. ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. አቶ ተግባሩ ሽፌ አበበ የተባሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ የእህታቸውን ባል ተዝካር (የ“ፋኖ” አባል የነበረ) ታድመው ከደባይ ጥላትግን ወረዳ ሲመለሱ፣ በቁይ ከተማ አሰንዳቦ ፍተሻ ኬላ ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። ግድያው የተፈጸመባቸው ሲፈተሹ የሟችን ፎቶግራፍ ይዘው በመገኘታቸው “ለምን ፎቶውን ይዘህ ተገኘህ?” በሚል እንደሆነና እስከ ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. እኩለ ቀን ድረስ አስከሬናቸው እንዳይነሳ ከልክለው እንዳቆዩት የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል። 
  21. ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በማእከላዊ ጎንደር ዞን፣ ጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ለምባ አርባይቱ ቀበሌ፣ አርባ ተንሳይ ጎጥ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመግባት በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኝ ሕጋዊ የጦር መሣሪያ ከሰበሰቡ በኋላ አቶ ነጋ ያለው (75 ዓመት)፣ አቶ አጉማሴ አዱኛ (45 ዓመት) እና አቶ ታእት ታከለ (34 ዓመት) የተባሉ 3 ሰዎችን ሕዝብ በተሰበሰበበት እንደገደሏቸው የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞች አስረድተዋል። 
  22. ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ብልባላ ከተማ በተፈጸመ የድሮን/የአየር ጥቃት እማሆይ ደስታ ካክራው የተባሉ የ83 ዓመት አረጋዊት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተገድለዋል። በዚሁ ግቢ ውስጥ ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ 2 የብልባላ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ጥቃት ከመድረሱ በፊት እና ከደረሰ በኋላ በአካባቢው የድሮን ድምጽ ይሰማ እንደነበር ለማወቅ ችሏል። 
  23. ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ እናርጅ እናውጋ ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የተከሰተውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ቡሽት ኮኛ ቀበሌ፣ ግራርጌ ሰፈር በመጫወት ላይ ከነበሩ ሕፃናት መካከል ባንችግዜ አዲስ በተባለች የ5 ዓመት ሕፃን ላይ ሞት እና እባብሰው ጌቴ በተባለ የ6 ዓመት ሕፃን ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በተመሳሳይ ቀን በዚሁ ቀበሌ በሌላ መንደር በተፈጸመ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ጥቃት ወይዘሮ መደሰት ሞኜ የተባሉ የ42 ዓመት ሴት የሞቱ ሲሆን 1 ወጣት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኝ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።  
  24. ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ ፋግታ ለኮማ ወረዳ፣ ፋግታ አጠቃላይ 1 ደረጃ ትምህርት ቤት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቁጥጥር ሥር የነበሩ 12 የመንግሥት የጸጥታ አባላት እና ለጸጥታ አባላቱ ምግብ አቅራቢ የነበሩ 2 ሴቶች (ወይዘሮ ፈንታነሽ መላኩ እና ወይዘሮ ይመኙሽ አንዱዓለም) በድምሩ 14 ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪም 9 በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ይገኙ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ አባላት፣ 1 ሕፃን (ከላይ በስም የተጠቀሱት የሟች ወይዘሮ ይመኙሽ አንዱዓለም የ2 ዓመት ሴት ልጅ) እና በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሻይና ቡና በመሸጥ የምትተዳደር 1 ሴት በአጠቃላይ 11 ሰዎች በጥቃቱ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የዐይን እማኞች አስረድተዋል። 
  25. ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ገነተ-ማርያም ቀበሌ አርክን በተባለ ልዩ ጎጥ ሲያመርቱ የዋሉትን የጤፍ ምርት ለመጠበቅ አውድማ ተኝተው የነበሩ 5 የአንድ ቤተዘመድ አባላት የሆኑ አርሶ አደሮች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንደተገደሉ የተጎጂዎች ቤተሰቦች ለኢሰመኮ አስረድተዋል። በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቀደም ብለው ከአካባቢው በመሸሻቸው የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሲገቡ አውድማው ላይ ተኝተው ያገኟቸውን በግጭት ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸውን አርሶ አደሮች እንደገደሏቸው ጨምረው ገልጸዋል።   
  26. ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደ ደብረ ኤልያስ ወረዳ በጭነት መኪና ተሳፍረው በመጓዝ ላይ የነበሩ የደብረ ኤልያስ ወረዳ የመንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት 2 ሴት ሠራተኞች ጎዛመን ወረዳ ውግር ቀበሌ ሲደርሱ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ከመኪና አስወርደው ከወሰዷቸው በኋላ በማግሥቱ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ተገድለው እንደተገኙ የሟች ቤተሰቦች አስረድተዋል። ሠራተኞቹ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ ደብረ ኤልያስ ወረዳ መግባታቸውን ተከትሎ ቀደም ሲል ወረዳው በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) ቁጥጥር ሥር በነበረበት ወቅት ለወራት ለቀው የነበሩት ሁሉም የወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ በተደረገው ጥሪ መሠረት በመመለስ ላይ የነበሩ ናቸው። የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ማስታወቂያ በወጣበት ወቅት የታጣቂ ቡድኑ (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት በበኩላቸው ሠራተኞች እንዳይመለሱ ያስጠነቀቁና ያስፈራሩ እንደነበር ኢሰመኮ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል። 
  27. በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሸካ ዞን አጎራባች ቀበሌዎች መካከል አልፎ አልፎ በወሰን አለመግባባት ምክንያት ግጭቶች የሚከሰቱ ሲሆን፣ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በዘለቀ ግጭት በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን፣ መንገሺ ወረዳ፣ የሪ ቀበሌ ጂፎር ንኡስ ቀበሌ ውስጥ 5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። እንዲሁም የተወሰኑ ነዋሪዎች የቤት ውስጥ ዕቃዎችን እና የእርሻ ሥራ መሣሪያዎችን ጨምሮ ንብረት  ተዘርፏል።  
  28. በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሳጃ ወለል ወረዳ፣ የላሎ ገለታ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ዳግም ኢገዙ እና አቶ ጸጋ ተክሌ የተባሉ 2 ሰዎች ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ጋር “ግንኙነት አላችሁ፤ ስንቅ እና መረጃ ታቀብላላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ  በዚያው ዕለት ማለትም መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል። 
  29. መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣  አመያ ወረዳ ኢተያ ገምባ ጀቴ፣ ኢላላ እና ጢሮ ኢላላ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች “በአካባቢው ላለው የመንግሥት ጸጥታ ኃይል ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል አቶ አለኸኝ አባተ፣ አቶ ተመቸው አርቄ፣ አቶ በለጠ ከበደ፣ አቶ ተመስጌን ተፈራ እና አቶ አስፋ ርቀው የተባሉ 5 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፡፡  
  30. መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ኢተያ ገምባ ጀቴ ቀበሌ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አቶ ሙሳ ኑሩ፣ አቶ ኢብራሒም መሐመድ፣ አቶ ኢብራሒም ኡመር እና አቶ ጉልማ (ከ5 ቤተሰቦቹ ጋር) በአጠቃላይ 9 ሰዎችን ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) “ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል ገድለዋል።  
  31. ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቤጊ ወረዳ፣ የኮበሬ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ መሐመድ ሀጂ ጀማል የተባሉ ሰው ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) “ድጋፍ አድርገሃል” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች  ከተያዙ በኋላ በዕለቱ በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።  
  32. ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቆንዳላ ወረዳ፣ የወንዲ ዶች ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ምናለ ቃስም የተባሉ ሰው “ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ  በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል። 
  33. ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ንጋት ላይ በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ ብርቢሣ እና ጋሌ በተባሉ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት “የመንግሥት አካላትን ተባብራችኋል” በሚል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና አረጋዊያንን ጨምሮ 17 ወንዶች እና 21 ሴቶች በአጠቃላይ 38 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፤ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሲቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል። 78 መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥለዋል።   
  34. ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ መጃ ላሉ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት በቀበሌው በሚኖሩ የጉራጌ ብሔር ተወላጆች ላይ በምሽት ቤታቸውን በላያቸው ላይ በማቃጠል እና ጥይት በመተኮስ በአጠቃላይ 12 ሰዎችን ገድለዋል። 
  35. ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት 2፡00 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ በመቂ ከተማ 02 ቀበሌ ማንነታቸው በውል ባልታወቀ ነገር ግን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት መሆናቸው በተጎጂዎችና በተጎጂ ቤተሰቦች የተጠረጠሩ የታጠቁ አካላት በፈጸሙት ጥቃት 3 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን አንድ የ12 ዓመት ሕፃንን ጨምሮ 4 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል።
  36. ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በአርሲ ዞን፣ ሽርካ ወረዳ፣ ሶሌሳ ረከታ እና መከና ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ከሌሎች ነዋሪዎች ለይተው በፈጸሙት ጥቃት 13 ሰዎችን ከመኖሪያ ቤቶቻቸው በማስወጣት በጥይት ገድለዋል።  
    • የዘፈቀደ፣ ጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት 
  37. የዘፈቀደ እስር የሕግ መሠረት የሌለው እስር ሲሆን ተገቢነት የሌለው፣ ፍትሐዊ ያልሆነ እና ሕጋዊ ሥነ ሥርዓቶችን ያልተከተለ እስርን ይጨምራል። በትጥቅ ግጭት ወቅት ከሰላም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ሊያዙ እንደሚችሉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ድንጋጌዎች ቢያስቀምጡም በዚህ ወቅትም ቢሆን የሕጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነት፣ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ የመሆን የሰብአዊ መብቶች መርሖችን ባከበረ መልኩ መሆን ይኖርበታል። የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ፣ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑ ተለይቶ እንዲገለጽላቸው መብት አላቸው። የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት፣ በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት አላቸው። 
  38. በአማራ ክልል ከመስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የዘፈቀደ እና የጅምላ እስራቶች መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያስረዳሉ። ከታሰሩት ሰዎች መካከል በየደረጃው ያሉ የክልሉ የመንግሥት አመራሮች፣ የጸጥታ ተቋማት አመራሮች እና አባላት፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ሕግ፣ የምክር ቤት አባላት፣ ነጋዴዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የ1 እና 2 ደረጃ ትምህርት ቤት እና የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ በግል ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአብነት (የቆሎ) ተማሪዎች ይገኙበታል። ከተያዙ ሰዎች ውስጥ ጥቂት ሰዎች ከሰዓታት ወይም ከቀናት እስር በኋላ ሲለቀቁ ከ6ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጊዜያዊ ማቆያነት /መደበኛ ያልሆኑ/ በተመረጡ 4 ቦታዎች (ዳንግላ፣ ጭልጋ (ሰራባ ወታደራዊ ካምፕ)፣ ኮንቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች) ታስረው ይገኛሉ። ከተያዙት ሰዎች መካከል ክስ እንዲመሠረትባቸው የተወሰነባቸው ጥቂት ሰዎች ከጊዜያዊ ማቆያ ማእከላቱ ወደ ማረሚያ ቤቶች ተዛውረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ከመደረጉ እና በዳንግላ ማቆያ ማእከል የሚገኙ የተወሰኑ እስረኞች ጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ከመለቀቃቸው በስተቀር፣ በርካታ ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ዕለት ድረስ ታስረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። 
    • አስገድዶ መሰወር፣ እገታ እና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ ሰዎችን አስሮ ማቆየት 
  39. አስገድዶ መሰወር፣ እገታ እና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ ሰዎችን አስሮ ማቆየት በሕይወት ከመኖር፣ ከጭካኔ እና ኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ፣ ፍትሕ የማግኘት እና ሌሎች መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥበቃዎችን የሚጥሱ ተግባር ናቸው። አስገድዶ መሰወር በመንግሥት ወኪሎች ወይም ከመንግሥት ፈቃድ ወይም ድጋፍ በተሰጣቸው ሰዎች ወይም ቡድኖች ወይም በመንግሥት ስምምነት አንድን ሰው በማሰር፣ አፍኖ በመውሰድ፣ ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ ነጻነቱን በመንፈግና በቁጥጥር ሥር መዋሉን በመካድ፣ በመደበቅ፣ ያለበትን ቦታ ባለማሳወቅ ወይም ደብዛውን በማጥፋት ፈጽሞ ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆን ማድረግ ነው። ዓለም አቀፍ ባልሆነ ጦርነት ጊዜ የተጥቅ ትግሉ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች አስገድዶ መሰወርን ለመከላከል የተያዙ ሰዎችን የመመዝገብ እና ድኅንነታቸውን የማስጠበቅ ግዴታ አለባቸው። መንግሥታት በማንኛውም ጊዜ ሰዎችን በታጠቁ ኃይሎች እና ቡድኖች ከአስገድዶ መሰወር እና ከመታገት የመጠበቅ ኃላፊነትም አለባቸው።  
  40. በአማራ ክልል፣ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብርሃም ዘሪሁን ከመኖሪያ ቤታቸው በክልሉ አድማ ብተና ፖሊስ አባላት ተይዘው ሙሉዓለም የባሕል ማእከል በሚገኘው የአድማ ብተና ጊዜያዊ ካምፕ የተወሰኑ ቀናት ቆይተው በተለምዶ “መኮድ” ተብሎ ወደሚጠራው የመካለከያ ካምፕ ከተዛወሩ በኋላ ያሉበት ሁኔታና ቦታ ሳይታወቅ ቆይቶ ከታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ዳባት ከተማ በሚገኘው የተሐድሶ ስልጠና ማእከል እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል።   
  41. ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት ላይ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቡሬ ከተማ፣ ታደሰ ገድፍ ዓለሙ እና ዘላለም ጥላሁን የተባሉ ሰዎች ከሚኖሩበት ቡሬ ከተማ በከተማው ፖሊስ አባላት ተይዘው ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ ሰዎቹ የትና በምን ሁኔታ እንዳሉ ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ማወቅ አልተቻለም።   
  42. ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ጣርማ በር ወረዳ፣ መሃል አምባ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የአዲስ አበባ ማእከል ሪፖርተር የሆኑትን አቶ ሳሙኤል ኪሮስን ኮምቦልቻ ደርሰው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ መሃል አምባ በተባለ ቦታ ላይ አግተው እንደወሰዷቸው የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል። ወደተጎጂው የእጅ ስልክ ደውለው እንዳነጋገሯቸው፣ ታጣቂዎቹን በስልክ አግኝተው ሲጠይቋቸው “ጋዜጠኛውን በሙያ ምክንያት ለሥራ እንደሚፈልጉትና እንደማይለቁት” እንደነገሯቸው ቤተሰቦቻቸው ጨምረው ገልጸዋል። ጋዜጠኛው የዕረፍት ጊዜ ወስደው ቆይተው ወደ ሥራ ገበታቸው ሳይመለሱ ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ደውለው “ታግቻለሁ” ብለው ሪፖርት እንዳደረጉ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአሚኮ የሥራ ክፍል ኃላፊ አስረድተዋል። የተጎጂ ቤተሰቦች በእገታው ከደረሰባቸው ጭንቀትና የሥነ ልቦና ጉዳት በተጨማሪ ከእገታው ጊዜ (ኅዳር ወር 2017 ዓ.ም.) ጀምሮ የተጎጂው የደመወዝ ክፍያ የተቋረጠ በመሆኑ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር መጋለጣቸውን ለኢሰመኮ ገልጸዋል። 
  43. ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በሰሜን ወሎ ዞን፣ ወልድያ ከተማ ሚፍታህ አሚኑ የተባሉ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ የ30 ዓመት ወጣት በመንግሥት የጸጥታ አባላት “ጥይት ትነግዳለህ” በሚል ጥርጣሬ ከሥራ ቦታቸው ተይዘው “ኢንዱስትሪ መንደር” በሚባለው ቦታ ታስረው ከቆዩ በኋላ ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ያሉበት ቦታና ሁኔታ አይታወቅም። 
  44. ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ምሕረቱ ትእዛዙ ከመኖሪያ ቤታቸው እንደወጡ በመንግሥት የጸጥታ አባላት ተይዘው “መኮድ” ተብሎ በሚጠራው የመከላከያ ካምፕ ውስጥ እንደቆዩና ከአንድ ሳምንት በኋላ ግን ወዳልታወቀ አካባቢ ተወስደው ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ያሉበት ቦታና ሁኔታ አይታወቅም፡፡  
  45. ታኅሣሥ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ባሕር ዳር ከተማ፣ ቀበሌ 15 ነዋሪ የሆኑት ቴዎድሮስ ጌታቸው በመንግሥት የጸጥታ አባላት ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው ወደ አልታወቀ ቦታ ተወስደው፤ ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም።  
  46. በኦሮሚያ ክልል ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ዋጫሌ ወረዳ፣ ካራ እና በቾ በተባለ ስፍራ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት ባደረሱት ጥቃት የተገደሉ የአስተዳደርና የጸጥታ አካላትን አስከሬን እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ያነሱ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ የአካባቢው ነዋሪዎችን ታጣቂዎቹ እንዳገቱ ለማወቅ ተችሏል። 
    • የሀገር ውስጥ መፈናቀል 
  47. የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በትጥቅ ግጭት፣ በመጠነ ሰፊ ብጥብጦች፣ በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወይም በሌላ ማንኛውም ሰው ሠራሽ ወይም የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ወይም በሚያስከትሏቸው ውጤቶች የተነሳ ከሚኖሩበት ቤት ወይም ከመደበኛ የመኖሪያ ቦታቸው እንዲሸሹ ወይም ለቀው እንዲወጡ የተገደዱ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለውን የሀገራት ድንበር ተሻግረው ያልተሰደዱ ሰዎች ወይም ቡድኖች ናቸው። 
  48. በአፋር ክልል እና ሶማሊ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማቆም በሐምሌ አጋማሽ 2016 ዓ.ም. የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ስምምነት ካደረጉ ወዲህ ግጭቱ እንደቆመ ለመገንዘብ ተችሏል። በክልሎቹ መካከል በነበረው ግጭት በሁለቱም ወገን ተይዘው የቆዩ ሰዎች ልውውጥ በኅዳር ወር መጨረሻ 2017 ዓ.ም. ተደርጓል። በተጨማሪም የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶችና ዕርቀ ሰላም በማካሄድ የሁለቱን ሕዝቦች አብሮነት ለማጠናከር መታቀዱን ለመረዳት ተችሏል። ይሁንና በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች መሠረታዊ አገልግሎት፣ በቂ ሰብአዊ ድጋፍ ከማቅረብ እና ዘላቂ መፍትሔ (durable solution) ከማበጀት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ኢሰመኮ ተገንዝቧል። 
    • የመዘዋወር ነጻነትና መጓጓዣ ላይ የተጣሉ ሕገወጥ ገደቦች  
  49. በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ባስተላለፉት ትእዛዝ መሠረት በክልሉ የሚገኙ አብዛኞቹ መስመሮች ከመስከረም 23 እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ተዘግተው ከቦታ ቦታ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቋርጦ መቆየቱን፣ እንደገና ከኅዳር 30 እስከ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. የጎጃም አካባቢ ዋና ዋና መስመሮች በታጣቂዎች አማካኝነት በመቋረጣቸው የኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተገድቦ እንደቆየ ኢሰመኮ ባደረገው ክትትል ለመረዳት ችሏል። 
    • የዳኝነት ነጻነት መሸርሸር 
  50. የዳኝነት ነጻነት ተቋማዊና ግለሰባዊ ነጻነትን ያካትታል። በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79 (2) መሠረት በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የዳኝነት አካላት ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ባለሥልጣንም ሆነ ሌላ ተጽዕኖ ነጻ ናቸው። ግለሰባዊ ነጻነት ዳኞች ካለምንም ጣልቃ ገብነት፣ ተጽዕኖና ግፊት የቀረበላቸውን ጉዳይ ሕግና ማስረጃን ብቻ መሠረት በማድረግ እንዲወስኑ ሙሉ ነጻነት ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት ነው። ዳኞች ሙያዊ ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጡ ዘንድ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ ከጥቃትና ትንኮሳ በሕግ እንዲሁም በተግባር ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። የዳኝነት ነጻነት መከበር የግለሰብ መብቶችን ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰዎች የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሣሪያ ነው።   
  51. በአማራ ክልል በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚሠሩ ዳኞች ከዳኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ  በሚሰጡት ውሳኔና ትእዛዝ ሳቢያ በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ሕገ ወጥ እስራት፣ ጥቃት፣ ማስፈራራት እና ጣልቃ ገብነት እንደሚፈጸምባቸው እንዲሁም ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ውሳኔና ትእዛዝ አለማክበር እንደሚስተዋል ኢሰመኮ ለማረጋገጥ ችሏል። 
  52. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት 22 ዳኞች እንዲሁም አዋጁ ካበቃ በኋላ 13 ዳኞች በአጠቃላይ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ  ውስጥ 35 ዳኞች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊነትን እና “የሕግ ማስከበር ዘመቻን” እንደ ሽፋን በመጠቀም ሕገ ወጥ እስራት ተፈጽሞባቸዋል። ለምሳሌ ከመስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2 ዳኞች፣ የባሕር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤት 2 ዳኞች፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1 ዳኛ፣ በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት 1 ዳኛ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን የቀወት ወረዳ ፍርድ ቤት 2 ዳኞች፣ የሸዋ ሮቢት ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት 1 ዳኛ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞርን ደጀን ወረዳ ፍርድ ቤት 1 ዳኛ እንዲሁም እነብሴ ሳር ምድር፣ ዳባት እና ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች (3 ዳኞች) በድምሩ 13 ዳኞች ከችሎት ላይ በጸጥታ አካላት ተይዘው ታስረዋል። ከታሰሩት ዳኞች መካከል 4 ዳኞች ከ10 ቀናት እስር በኋላ ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የተፈቱ ሲሆኑ ቀሪ 9 ዳኞች ይህ ሪፖርት እስተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ። ከፌዴራል እና ከሌሎች ክልሎች ሕጎች አንጻር የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 282/2014 የዳኝነት ነጻነትን ከማረጋገጥ አንጻር  እንደ አንድ ዋስትና የሚወሰደውን የዳኞች ያለመከሰስ መብት ጥበቃ አለማድረጉ በክልሉ እየታየ ላለው የዳኞች እስር እና ወከባ በር የከፈተ መሆኑን መረዳት ተችሏል። 
  53. ከእስራት በተጨማሪ ዳኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው  ለማወቅ ተችሏል። ለምሳሌ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ፍርድ ቤት 1 ዳኛ ችሎት ላይ እንዳሉ የጸጥታ አካላት የጦር መሣሪያ ደግነው ወደ ችሎት በመግባት “የኮማንድ ፖስት እስረኛ የሆነውን ተጠርጣሪ ለምን በዋስትና ትለቃለህ” በማለት ዳኛውን ከችሎት በኃይል ወደ ውጭ በማውጣት በፍርድ ቤቱ ደንበኞችና ሠራተኞች ፊት ከፍተኛ ድብደባ በመፈጸም የአካል ጉዳት አድርሰውበታል። ይህ ሪፖርት ይፋ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ የድርጊቱን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎች እንደሌሉ ለማወቅ ተችሏል። 
  54. በክልሉ በዳኝነት ሥራ ቀጥታ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ ፍርድ ቤቶች ከዳኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ የሚሰጧቸውን ውሳኔዎችና ትእዛዞች ተቀብሎ ያለመፈጸም ችግር መኖሩን ለማረጋገጥ ተችሏል። ፍርድ ቤት በተለይ በክልሉ ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች በዋስትና እንዲፈቱ ትእዛዝ ሲሰጥ ተጠርጣሪዎችን ለመፍታት ፈቃደኛ ያለመሆን እንዲሁም የፍርድ ቤት ትእዛዝን ባላከበሩ የፖሊስ አባላት ላይ የሚሰጡ የቅጣት ውሳኔዎችን ያለመፈጸም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት የሚታይ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ መሆኑን ኢሰመኮ ተገንዝቧል። ለምሳሌ በሰሜን ወሎ ዞን፣ የሀብሩ ወረዳ ፍርድ ቤት ከከተማ ቦታ ክርክር ጋር በተያያዘ ውሳኔ የሰጠባቸውን ከ10 በላይ መዝገቦች  በይግባኝ ሥርዓት ታይተው ባልተሻሩበት ሁኔታ የአካባቢው ኮማንድ ፖስት (አስፈጻሚ አካላት) ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ ሕገወጥ ነው በማለት እንዳይፈጸም አግደዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በረኸት፣ ምንጃር ሸንኮራ እና ሀገረ ማርያም ወረዳ ፍርድ ቤቶች ለጸጥታ አካላት ቀለብ መዋጮ የፍርድ ቤቶች ኃላፊዎችን በማስፈራራትና በማሰር ከዳኞችና አስተዳደር ሠራተኞች ደመወዝ  ላይ ተቆርጦ እንዲከፈል እና የመንግሥት ድጋፍ ሰልፍ ተገደው እንዲወጡ ተደርጓል። 
  55. በኦሮሚያ ክልል በስፋት ተግባራዊ የሚደረገው የ“ወቅታዊ ሁኔታ (Haala Yeroo)’’ የመንግሥት ጸጥታና ሕግ አስከባሪ አካላት ለአካባቢው ሰላምና ጸጥታ እንቅፋት ናቸው ወይም ከጸረ ሰላም ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው፤ ለታጣቂዎች የሎጅስቲክስ ድጋፍ ያደርጋሉ ወይም የድርጅቶቹ አባላት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን ለመቆጣጠር በሚል የሚጠቀሙት አሠራር ነው።   
  56. “በወቅታዊ ሁኔታ” በሚል የተያዙ ሰዎች ጉዳይ በየደረጃው በተደራጁ የጸጥታ ምክር ቤቶች ውሳኔ መሠረት ብቻ የሚወሰን ሲሆን፣ ከነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ትእዛዞችን በመፈጸም ረገድ ከፍተኛ ጉድለት አለ። ፖሊስ ተጠርጣሪዎች የተፈቀደላቸውን የዋስትና መብት ተፈጻሚ ላለማድረግ በመጀመሪያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጉዳይ በተጨማሪ በአዲስ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረዋል ወይም አዲስ ወንጀል በመፈጸም ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት የፍርድ ቤት ትእዛዞችን በተደጋጋሚ የማይፈጽም መሆኑን ኢሰመኮ አረጋግጧል። ለምሳሌ በ2017 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የዱከም ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 06167 ቱፋ ባጫ ባልቻ ለተባለ ተጠርጣሪ እንዲሁም በሉሜ ወረዳ መጀመሪያ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር  119628  በእነ ሽመልስ ቱሉ ጌቱ አዱኛ ለተባሉ ተጠርጣሪዎች ዋስትና የፈቀደ እና የዋስትና መስፈርቶችን ያሟሉ ቢሆንም ፖሊስ ትእዛዞችን ለመፈጸም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ይህ ሁኔታ የሰዎችን የነጻነት እና የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲሁም የፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ሥልጣን እና ነጻነት የሚጥስ ነው። 
  57. ጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ያያ ጉለሌ ወረዳ አቶ ጂኔኑስ ነጋሳ የተባሉ የወረዳውን ዳኛ የኦሮሚያ ክልል የጸረ ሽምቅ ውጊያ ፖሊስ አባላት በወረዳው ፍታሌ ከተማ የሚገኝ ካምፕ ውስጥ በማስገባት ከቀኑ 6፡30 እስከ 10፡00 ድረስ የቆየ ከፍተኛ ድብደባ አድርሰውባቸዋል። ኢሰመኮ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት በዞኑ በርካታ ወረዳዎች በ2016 ዓ.ም. በዳኞች እና በዐቃብያነ ሕግ ላይ ለተጠርጣሪዎች ዋስትና ፈቅዳችኋል ወይም እንዲፈቀድ ተባብራችኋል በሚል እስራት፣ ድብደባ እና ማዋከብ ሲፈጸም የቆየ መሆኑን ገለጸው እስካሁን ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ያልተደረገ መሆኑን እና በዚህ ምክንያት ዳኞች ሕግ እና ህሊናቸው በሚፈቅደው መሠርት የዳኝነት ሥራዎቻቸውን በነጻነት ለመሥራት እንደተቸገሩ አስረድተዋል።  የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኛው ላይ የተፈጸመውን ድብደባ አስመልክቶ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።  
    • ምክረ ሐሳቦች 
  58. ኢሰመኮ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከቀጠሉ የትጥቅ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎችና የክትትል ሪፖርቶች የተካተቱና በከፊል ወይም በሙሉ ተፈጻሚ ያልሆኑ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ በድጋሚ ያሳስባል። በተለይም፦ 
    • በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ጅማሮ በማስፋት፣ መንግሥትን ጨምሮ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ፤ 
    • በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፤ በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤ እንዲሁም በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፤ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ፤ 
    • በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች የመዘዋወር ነጻነትና መጓጓዣ ላይ የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆኑ ገደቦችን ጨምሮ ኅብረተሰቡን ከሚያማርሩ እና ነጻነትን ከሚገድቡ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፤  
    • መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ በሚገኙት የትጥቅ ግጭቶች፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባላት ተጠያቂ ለማድረግ ተአማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር፤ እንዲሁም በግጭቶቹ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲያደርግ፤ 
    • በአማራና በኦሮሚያ ክልል “ከወቅታዊ ጉዳዮች” ጋር በተያያዘ በሚል የተያዙና ተአማኒ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ጉዳያቸው በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እንዲታይ፣ የመንግሥት የጸጥታና የአስተዳደር አካላት በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሰዎችን በመደበኛ ማቆያዎች ብቻ እንዲይዙና የተያዙ ሰዎች ያሉበት ቦታና ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው እንዲገለጽ፤  
    • የታጠቁ ቡድኖችን ጨምሮ በ3ኛ ወገኖች ከእገታ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እንዲሁም የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እና የተጎጂዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ውጤታማ እርምጃዎችን እንዲወስድ፤  
    • ዳኞች ከዳኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ በፍትሐ ብሔርም ሆነ በወንጀል ጉዳዮች ያለመከሰስ መብት የሕግ ዋስትና (ከለላ) እንዲሰጣቸው፣ በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት በፍርድ ቤቶች አሠራር ጣልቃ ከመግባት እንዲሁም የፍርድ ቤቶችን ውሳኔና ትእዛዝ የማያከብሩ እንዲሁም በዳኞች ላይ እስራት የፈጸሙ የፖሊስ እና የጸጥታ አካላት ላይ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የሚወሰደው እርምጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ እንዲሁም 
    • በአፋር ክልል እና ሶማሊ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ለተፈናቀሉ ሰዎች መሠረታዊ አገልግሎት፣ በቂ የሆነ እና አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ፣ ለመፈናቀል ምክንያት የሆነው የጸጥታ ሥጋት ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ የተጀመሩ እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል።